በተግባር እየተገለጠ ያለው የትውልድ ድምፅነት

You are currently viewing በተግባር እየተገለጠ ያለው የትውልድ ድምፅነት


• አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የከተማዋን ትናንት በወጉ ሰንዶ፣ ዛሬዋን በልኩ ቀምሮ ነገዋን አሻግሮ በመመልከት ከፍታዋን ለማስጠበቅ እየሰራ
መሆኑ ተመላክቷ

አዲስ አበባ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን አሻግረው በሚያሳዩ አስደማሚ ህንፃዎች፣ በታሪካዊ ስፍራዎች እና በልዩ ልዩ ቅርሶች ያሸበረቀች ውብ ከተማ ናት። ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን የሚያምር ማንነታቸውን በጠንካራ አንድነታቸው ሸምነው በፍቅር የሚኖሩባት ማዕከል ናት፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ደግሞ በህትመት፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥን እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አውታሮቹ እንደ ስሟ እየፈካች ያለችውን ከተማ፣ ትናንቷን በወጉ ሰንዶ፣ ዛሬዋን በልኩ ቀምሮ ነገዋን አሻግሮ በመመልከት ከፍታዋን ለማስጠበቅ እየሰራ ነው። በስራው ጥራትን፣ ፍጥነትን እና የላቀ አክብሮትን ምርኩዝ አድርጎ ሰላምና ልማትን፣ ተዝናኖት እና ቁም ነገርን በየፈርጁ እየከሸነ የትውልድ ድምፅነቱን እያስመሰከረ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርቡ በከተማም ሆነ በሀገራዊ ልዩ ልዩ ጉዳዮች ላይ ባሳየው ትጋት ያገኛቸው እውቅናና ሽልማቶች ምስክር ናቸው፡፡

በእርግጥም እንደ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ያሉ ተቋማት ከተሞች ከስልጣኔ ጋር እንዲወዳጁ፣ የብዝሃነት ማዕከልነታቸው ለዛና ውበቱን ጠብቆ እንዲቀጥል፣ ያለፈውን በትውስታ፣ ያለውን በጥበብ  እንዲሁም መጭውን  በተስፋ  እያስዋቡ ለመጓዝ ያላቸው ድርሻ ከፍ ያለ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ይናገራሉ፡፡

ለዚህ ደግሞ የሊድስ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ተባባሪ ፕሮፌሰሯ ጆርጂያ አይኤሎ፣ በጄኔቫ ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ማትዮ ታራንቲኖ እና በሊድስ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት የባህል ፖሊሲ ፕሮፌሰር ኬት ኦክሌይ በጋራ ባሳተሙት “Communicating the City” የተሰኘውን መፅሐፍ በአስረጂነት ማቅረብ ይቻላል፡፡

በመፅሐፉ ላይ በሰፈረው ሀሳብ መሰረት በአስደማሚ ውበትና ጥበብ፣ ከከተሞች የህንፃ፣ የመንገድ እና መሰል መሰረተ ልማቶች እንዲሁም ብዝሃ መገለጫ ያላቸው ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ልዩነታቸውን እንደ ውበት ደምቀውበት አንድነታቸውን ደግሞ ለሁለንተናዊ ከፍታቸው እንደ ብርቱ ምሰሶ ተጠቅመውበት እንዲኖሩ ለማስቻል ከምንም በላይ የሚዲያ ጉልበት ከፍ ያለ ነው፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት በከፍተኛ የለውጥ ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል፡፡ ዋርካና አገልጋይን በመሳሰሉ የቴሌቪዥን፣ የህትመት፣ የሬዲዮ እና የማህበራዊ ሚዲያ ስራዎቹ ወደ ህብረተሰቡ ልብ የቀረበ በመሆኑ በየጊዜው ተወዳጅነቱና ተመራጭነቱ እየጨመረ በመምጣቱ ከተለያዩ ተቋማት “የአብረን እንስራ” ጥያቄዎች እየቀረቡለትና ስምምነቶችንም በየጊዜው በማድረግ ላይ ነው፡፡

ለአብነትም ባሳለፍነው ሐሙስ  በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና በአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የተደረገው ስምምነትን በዋቢነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ ስምምነቱ በተደረገበት ወቅትም የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ እና የቴሌቪዥን ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጥላሁን ካሳ፣ ሚዲያው የተለያዩ የልማት እና መሰል ሀገርን እና ማህበረሰብን የሚጠቅሙ ስራዎች የጋን ውስጥ መብራት ሆነው እንዳይቀሩ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል፡፡

በመሆኑም ከተቋሙ ጋር የተደረገው ስምምነት በቴሌቪዥን ብቻ ሳይሆን በአንጋፋዋ አዲስ ልሳን ጋዜጣ፣ በኤፍ.ኤም 96.3 እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያው በኩል ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ጋር አብረን እንሰራለን ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ሁለቱ ተቋማት በቤተሰብነት አብረው እንደሚሰሩ ጠቁመዋል፡፡ አክለውም፣ ስራዎቹን ከማስተዋወቅ ባሻገርም የትውልድ ድምፅ የሆነው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሚዲያ አቅም ያለው በመሆኑ ሌሎችም እንደ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በመምጣት ልምድ የሚወስዱበትንም ዕድል የሚፈጥር ስምምነት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ በበኩላቸው፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ስለ አካባቢ ጥበቃ ልምድና ዕውቀት ያላቸውን ምሁራን በመጋበዝ የተሰሩ ስራዎች በተሻለ ሁኔታ ለህዝብ ጆሮ የሚደርሱበት እና የአካባቢ ጥበቃ ዘመን መሆኑን የሚያሳይ እንዲሁም መንግስት ለአካባቢ ጥበቃ በሰጠው ትኩረት ልክ  ሚዲያው ሽፋን እንደሚሰጠው እናምናለን ብለዋል። አክለውም፣ ፅዱ ኢትዮጵያን ባህል እናድርግ የሚለው ንቅናቄ ውጤታማ እንዲሆን አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለውም መስክረዋል፡፡

ከዚህ በፊትም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የከተማዋ የቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ ስራና ክህሎት ቢሮ፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርትና በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል፡፡

ሚዲያው ከተቋማት ጋር በአደረጋቸው ሌሎች ስምምነቶች መካከል የአዲስ አበባ ስራና ክህሎት ቢሮ ጋር ያደረገው ስምምነት የሚታወስ ነው፡፡ ተቋማቱ በጋራ ለመስራት የተስማሙት “የሚሰሩ እጆች ወግ” የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ሲሆን፣  የስራ ባህል ለማዳበር ብሎም በቂ የስራ ዕድል የሚፈጠርበትን መደላድል መፍጠርን ያለመ ስለመሆኑም በተፈራረሙበት ወቅት መገለፁ ይታወሳል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review