“የፕሮጀክቱ አፈጻጸም መጓተት በእንቅስቃሴያችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል”
ነዋሪዎች
“ፕሮጀክቱ በበጀት ዓመቱ ተጠናቅቆ ወደ አገልግሎት እንዲገባ ይደረጋል”
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣን
ውድ አንባቢያን፤ ስለአየር ጤና ወለቴ ሱቅ – አለምገና አደባባይ አስፋልት ግንባታ ፕሮጀክት በመጋቢት 27 ቀን 2017 ዓ.ም ዕትማችን መዘገባችን ይታወሳል። በወቅቱም የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 10 በመቶ እንደነበር ተመላክቷል፡፡ ለመሆኑ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም አሁን ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? ሲል የዝግጅት ክፍላችን የአካባቢውን ነዋሪዎች፣ የፕሮጀክቱን የስራ ተቋራጭ፣ አማካሪ መሀንዲስ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለስልጣንን አነጋግሯል፡፡
ወይዘሮ ሳራ ታደሰ በአጃምባ ኮንዶምንየም መኖር ከጀመሩ 5 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የመንገድ ግንባታ ስራው ከመጀመሩ በፊት ከአየር ጤና እስከ ካራ ለመድረስ ከአንድ ሰዓት በላይ ይፈጅ ነበር፡፡ ለምሳሌ፡- ማታ ከስራ ቦታ 11፡45 ሰዓት ተነስተን እስከ ሩብ ጉዳይ ለሁለት ድረስ እናመሽ ነበር። ጠዋትም ቢሆን ሰርቪስ ካመለጣቸው በትራንስፖርት በሰዓቱ ስራ ቦታ መድረስ እጅግ በጣም ፈታኝ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ከስራ ኃላፊዎቻቸው ጋር ግጭት ውስጥ እንዲገቡ ያደርጋቸው ነበር። ቅዳሜና እሁድም ቢሆን በማህበራዊ መስተጋብራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድር ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት የግል መኖሪያ ቤታቸውን አከራይተው ወደሌላ ሰፈር ተከራይተው ለመኖር ውሳኔ ላይ ደርሰው እንደነበርም ያስታውሳሉ፡፡ የመንገድ ስራው ከጀመረ ከ2016 ዓ.ም ወዲህ በተለይም ከአየር ጤና እስከ ካራ ድረስ ግማሹ የመንገድ ክፍል የአስፋልት ስር ንጣፍ እንዲሁም ድልድዮች በመሰራታቸው የትራንስፖርት ችግሩ መሻሻል አሳይቷል፤ የግል ቤታቸውን ትትው ከመከራየት ታድጓቸዋል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጪያችን በጫማ ንግድ የተሰማራችው ወይዘሪት ሳራ ሀሰን ናት፡፡ መንገዱ ከተቆፋፈረ ወዲህ በስራዋ ላይ እንቅፋት እንደፈጠረባት ትገልጻለች። በበጋ አቧራው የጫማዎቹን አዲስነት በመቀነስ ዋጋ እንዲያጣ አድርጎባታል። ከዚህ በተጨማሪ በመቆፋፈሩ ሱቋ ዳገት ላይ እንዲንጠለጠል፣ መውጫ መግቢያ መንገዱ ገደልና ጭቃ እንዲሆን በማድረግና በዚህም የተነሳ ደንበኞቿን እንዳሳጣት ነው የምትገልጸው፡፡ አሁን ላይ ኪሳራ ውስጥ መግባቷን ገልጻ “የመንገድ ስራው ሲጠናቀቅ በአዲስ ስራ እጀምራለሁ” በሚል በተስፋ እየጠበቀች እንደሆነ ነው የገለጸችው፡፡
በአካባቢው በትራፊክ ማስተናበር ተሰማርተው ያገኘናቸው ሳጂን አዲስ አስረስም ስለመንገዱ አስተያየት ሰጥተውናል፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ በዚህ መስመር መስራት ከጀመሩ አንድ ዓመት አስቆጥረዋል፡፡ መጀመሪያ ላይ ሲመጡ መንገዱ ጠባብ ከመሆኑም በተጨማሪ ሌላ ምንም አይነት አማራጭ የሌለው ከመሆኑ የተነሳ የትራፊክ ፍሰቱ እጅግ በጣም አስቸጋሪ፣ በተለይም በሰው ህይወትና አካል እንዲሁም በንብረት ላይ ጉዳት ይደርስ ነበር፡፡ የማስተናበር ስራውን ያለእረፍት ከጠዋት እስከ ማታ ድረስ መሀል ላይ ቆመው ለመስራት ይገደዱም ነበር፡፡
በሂደት የመንገዱ የትራፊክ ፍሰት መሻሻል አሳይቷል፡፡ አሁን ላይ ከአየር ጤና እስከ ካራ አጃንባ መገንጠያ የሚገኘው ግማሽ የመንገድ ክፍል ላይ አንጻራዊ ለውጥ እየመጣ ነው፡፡ ሙሉ በሙሉ የመንገድ ስራው ካልተጠናቀቀ በትራፊክ ፍሰቱ ላይ አሉታዊ ጫና ማሳደሩ ስለማይቀር በተቻለ መጠን ትኩረት ተሰጥቶት በፍጥነት ቢሰራ መልካም ነው ብለዋል፡፡
ካራ ቆሬ ተወልዶ ያደገበት ሰፈር እንደሆነ የሚገልጸው የራይድ አሽከርካሪ ወጣት አሚት ተስፋየ የመንገዱን አስቸጋሪነት ሲገልጽ፤ “እጅግ በጣም ይዘጋጋ ነበር፡፡ በተለይም ሁለት ሰዓት ካለፈ በኋላ ከካራ መውጣት ይከብድ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ከወጣሁ ማታ አራት ሰዓት ካልሆነ በስተቀር አልመለስም። በመንገዱ መጨናነቅ ምክንያት ሳልፈልግ አመሽ ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ ከመጣሁ ደግሞ በውስጥ ለውስጥ መንገድ ስለምጓዝ መኪናዬ እየተጎዳብኝ፣ ለአላስፈላጊ ወጪም ስዳረግ ቆይቻለሁ” ይላል፡፡ የመንገዱ የተወሰነ አካባቢ ስራ ከጀመረ ወዲህ የትራፊክ መጨናነቁ ቀለል ማለቱንም አክሏል፡፡
የጋዜጣዋ የዝግጅት ክፍል የፕሮጀክቱ አሁናዊ አፈጻጸም ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? ሲልም የፕሮጀክቱን ተጠሪ መሀንዲስ ኢንጂኒየር ሰውነት ተሰራን አነጋግሯል፡፡ እንደ ኢንጂኒየር ሰውነት ገለጻ፤ ፕሮጀክቱ የተጀመረው መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም ነው፡፡ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የሚፈጀው 1 ቢሊዮን 302 ሚሊዮን ሰባት መቶ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ሰባት ብር ነው፡፡ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ወደ ስራ ቢገባም በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ 243 ቀናት (ስምንት ወር ከሶስት ቀናት) ተጨማሪ የማጠናቀቂያ ጊዜ ተሰጥቶት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የመንገዱ አጠቃላይ ርዝመት 5 ነጥብ 67 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3 ነጥብ 4ቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ቀሪው 2 ነጥብ 27ቱ በሸገር ከተማ አስተዳደር ውስጥ ይገኛል፡፡ የመንገዱ ጠቅላላ ስፋት 30 ሜትር ነው፡፡ የአስፋልት ስራው ከሌሎች የአስፋልት ስራዎች በተለየ ጥራት ባለው ሁኔታ እየተሰራ ነው፡፡
የአስፋልት ስር ንጣፍ(sub base) የተሰራው ከሌላ የመንገድ ስራ በተለየ በጠጠርና በሬንጅ ቅልቅል መሆኑን ለጥራቱ በማሳያነት ተጠቅሷል፡፡ የተለመደው የመንገድ ስራ የአስፋልት ስር ንጣፍ(sub base) የሚሞላው ከጠጠር ብቻ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኘው የመንገዱ ክፍል ላይ የፍሳሽ ትቦ ቀበራ፣ የድጋፍ ግንብ ግንባታ፣ የውሀ መውረጃ ንጣፍ፣ የአስፋልት ስር ንጣፍ (sub base) የመሳሰሉ ስራዎች በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም በተወሰነ ደረጃ የትራፊክ መጨናነቁን ማስተንፈስ ተችሏል፡፡ አሁን ላይ ያለው የፕሮጀክት አፈጻጸም 12 ነጥብ 36 ደርሷል፡፡
የወሰን ማስከበር ችግር(እንደ የቴሌ እና የመብራት የመሬት ውስጥ መሰረተ ልማት፣ የህንጻዎች፣ የቤቶችና አጥር እንዲሁም የኤሌክትሪክ ምሰሶ አለመነሳት) አፈጻጸሙን ከዚህ በላይ ማሳደግ ላለመቻሉ በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መንገዱ ከወሰን ማስከበር ነጻ ባለመደረጉ የፕሮጀክቱ ውል ከተፈረመበት ነሀሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም እስከ ነሀሴ 5 ቀን 2015 ዓ.ም ባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ለስራ ተቋራጩ አስረክቦ ስራ ማስጀመር ሳይቻል መቆየቱንም ነው ኢንጂኒየር ሰውነት የገለጹት፡፡
ግንባታውን እያከናወነ የሚገኘው የይርጋለም ኮንስትራክሽን ስራ ተቋራጭ ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ ኢንጂኒየር ገብረስላሴ ከሀሰ፤ ድርጅቱ እንደ የጠጠር መፍጫ እና የአስፋልት መስሪያ ማሽን፣ የቱቦ ማምረቻ ቦታ ወስዶ እና በቂ ዝግጅት አድርጎ በጥራትና በፍጥነት ለመስራት ወደ ስራ የገባ ቢሆንም ወሰን ማስከበሩ በፍጥነት ባለመጠናቀቁ በተደረገው ዝግጅት ልክ ስራውን ማስኬድ አልተቻለም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ከፕሮጀክቱ አጠቃላይ 5 ነጥብ 67 ኪሎ ሜትር ውስጥ ከወሰን ማስከበር ነጻ የነበረው መንገድ 800 ሜትር ብቻ እንደነበረና በሂደት ቀሪው ነጻ ይሆናል በሚል ወደ ስራ መግባቱን አክለዋል፡፡
ስራ አስኪያጁ አያይዘው እንደገለጹት፤ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኘው 3 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመንገዱ ሽፋን ውስጥ በቀኝ በኩል 2 ኪሎ ሜትሩ በወሰን ማስከበር ተይዟል። በሸገር ከተማ አስተዳደር ስር የሚገኘው 2 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የዲዛይን ክለሳ ተደርጎበት ግንቦት ወር 2017 ዓ.ም ላይ የተሰጣቸው ቢሆንም ሙሉ በሙሉ የግራና ቀኙ የቴሌኮምና የመብራት ኃይል የወሰን ማስከበር ችግሩ አልተፈታም። በዚህ ሁኔታ ጊዜው እየተራዘመ መጥቶ አሁን ላይ የግንባታ ግብአት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ ስራው ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለመንገድ መስሪያ ሶስት አራት ማሽኖችን በማስገባትና በማስወጣት ለሌላ ተደማሪ ኪሳራ ተዳርጓል፡፡ ምክንያቱም አሁን ላይ የሚቆፈርም፣ የሚሞላም፣ የቱቦ መቅበር ስራ የለም፡፡ ይህ እየተንከባለለ የመጣው ችግር ለ2018 ዓ.ም እንዳይዘልቅ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው አፋጣኝ ምላሽ ቢሰጡ ለብዙዎች ቅሬታ ሆኖ የቆየውን ችግር መፍታት ይቻላል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
በታሰበው ልክ የመንገድ ስራውን ማፋጠን ባይቻልም እስካሁን ከአየር ጤና እስከ ካራ እንዲሁም ከአጃንባ መገንጠያ እስከ ወለቴ ደግነት ኮንዶምንየም ድረስ 830 ሜትር በግራ በኩል የአፈር ቆረጣ፣ የሙሌት ስራ፣ የውሀ ማፋሰሻ ቱቦዎች ቀበራ፣ የድልድይ ስራ ተከናውኗል። በፕሮጀክቱ ከሚገኙ 9 አነስተኛ ድልድዮች መካከል የ4ቱ ግማሽ ክፍላቸው ተጠናቅቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአየር ጤና እስከ ካራ ነጻ በሆነው የመንገድ ክልል ውስጥ የአፈር ቆረጣ ሙሌት የተጠናቀቀባቸውን ከአስፋልት ስር በታች የሚገኘውን የመሬት ክፍል ሙሌት ስራ ተሰርቷል፡፡ የእግረኛ የሸክላ ማንጠፍ ስራም እየተሰራ ነው፡፡ ቀሪውን አስፋልት የማንጠፍ ስራ የክረምቱ ዝናብ የሚወስነው በመሆኑ የአየር ጸባዩ ደረቅ የሚሆንበት ወቅት እየተጠበቀ ነው፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የሚያሰራው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ግንባታ ኮንትራት አስተዳደር ቡድን መሪ ኢንጂኒየር ዴሳዊ ሀዲስ የአየር ጤና ወለቴ ሱቅ – አለምገና አደባባይ አስፋልት ግንባታ መጓተት ምክንያትን አስመልክተው ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡን አስተያየት፤ “የፕሮጀክቱን ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ማጠናቀቅ አልተቻለም። ምክንያቱም አንደኛ የወሰን ማስከበር ስራው በወቅቱ አልተጠናቀቀም። ከዚህም በተጨማሪ የሸገር ከተማ አስተዳደር ከ አለም ገና አደባባይ ወደ ሰበታ የሚሄደውን የመንገድ ክፍል አዲስ አበባ ከሚገኘው መንገድ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን የዲዛይን ማስተካከያ መጠየቁ እና የክለሳ ስራው ተጠናቅቆ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላም የሚፈርሱና መነሳት ያለባቸው የመሬት ውስጥና ከመሬት በላይ የመብራት፣ የቴሌ፣ የውሀ መሰረተ ልማት እንዲሁም አጥር እና ቤቶች ያለመነሳት ችግሮች መኖራቸው ነው፡፡ ይህን የወሰን ማስከበር ችግር ለመፍታት ከሸገር ከተማ አስተዳደር ጋር የተግባቦት ስራ ተሰርቷል፡፡ ከጥራት ጋር ተያይዞም በግንባታ ወቅት የሚያጋጥሙ የተለያዩ ችግሮችን ከስር ከስር ማስተካከያዎች እንዲደረግ እንዲሁም ኮንትራክተሩ ነጻ በሆኑ መንገዶች ላይ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ አማካሪው በቅርበት እየተከታተለ ነው፡፡
መንገዱን ነጻ አድርጎ ኮንትራክተሩ በሙሉ አቅሙ ቀሪ ስራዎችን እንዲያጠናቅቅ ማድረግ የመንገዶች ባለስልጣን ኃላፊነት ከመሆኑ አንጻር የዝናብ ወቅቱ እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ የሚነሱ ነገሮችን ለይቶ ለሚመለከታቸው ተቋማት በማሳወቅ ተገቢውን የክፍያ ሰነድ እንዲልኩ፣ የላኩትንም ሰነድ በመፈተሽና በማረጋገጥ ክፍያውን በመፈጸም ነጻ የማድረግ ስራ ይሰራል” ብለዋል፡፡
በባለስልጣኑ የሬጉሌተሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂኒየር ፀጋዬ ቦርሴ በበኩላቸው፣ ከአዲስ አበባ ወደ ምዕራቡ የሀገራችን ክፍል መውጫ፣ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት ወሳኝ መንገድ ነው፡፡ ፕሮጀክቱን በፍጥነት አጠናቅቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ማድረግ ያልተቻለበት ምክንያት ከወሰን ማስከበር ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች እስከዛሬ ድረስ ባለመፈታታቸው ነው፡፡ የመሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት በተለይም መብራት ኃይል በመንገዱ በቀኝ በኩል የሚገኘውን የመብራት መስመር ለማንሳት የጠየቀው የካሳ ክፍያ ከነምንዛሬው የፕሮጀክቱን ግማሽ ዋጋ መጠየቁና ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ደግሞ የካሳ ክፍያውን እንዲቀንሱ ምክክር ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ይህ ረጅም ጊዜ ወስዷል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት መጨረሻ አካባቢ ማስተካከያ እንዲደረግ የተጠየቀውን የካሳ ክፍያ በመቀነሳቸው ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ በቅርቡ ክፍያውን በመፈጸም ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡
“ለፕሮጀክቱ መጓተት ከወሰን ማስከበሩ በተጨማሪ የስራ ተቋራጩ የስራ አፈጻጸም ድክመት ሌላው ምክንያት ነው” ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ነጻ የተደረጉትን ከስር ከስር አጠናቅቆ ያለማስረከብ ችግር አለበት፡፡ በዚህም ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል። የመጨረሻ አማራጭ ውለታውን ማቋረጥ ነው፤ ይህም በሂደት ቀጣይ በሚኖረው የስራ አፈፃፀም የሚታይ ይሆናል። ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያለውን አማራጭ አሟጥጦ መጠቀም ስላለበት በዚህ ደረጃ ስራውን ሲያስኬድ ቆይቷል፡፡ የ2018 በጀት ዓመት የክረምቱ ወቅት እንደተጠናቀቀ ወደስራ በመግባት ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት እንዲበቃ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡
በለይላ መሀመድ