በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል። ከዛሬ ጀምሮ ባሉት ቀናት ከሚቀርቡ መሰናዶዎች መካከል የሙዚቃ አልበም ምርቃት፣ የመጽሐፍት ህትመት፣ የሥዕል ዓውደ ርዕይ፣ የቴአትር መርሃ ግብር ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የዝግጅት ክፍላችን የተወሰኑትን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
“የግሬጌ ማስታወሻ ደብተር” የተሰኘ የትርጉም መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል። “diary of a wimpy kid” የተሰኘው ይኸ መጽሐፍ በተርጓሚ ፍሎረንስ አሰበ አማካይነት ወደ አማርኛ የተተረጎመ ነው፡፡ መጽሐፉ ልጆች የአማርኛ ንባብ እንዲያዳብሩና ስልቹ እንዳይሆኑ አድርጎ የሚያለማምድ የተባለ ሲሆን፣ በዋልያ መጽሐፍት አሳታሚ አማካይነት ታትሞ ለገበያ ቀርቧል፡፡
በሌላ ዜና “የህላዌ ዘለሰኛ” የተሰኘው የግጥም መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው። የፍቃዱ አስራት የግጥም ስብስቦችን የያዘው የህላዌ ዘለሰኛ መጽሐፍ 202 ገጽ ያለው ሲሆን፤ ወደ ማተሚያ ቤት መግባቱን ገጣሚው በማህበራዊ የትስስር ገጹ አስታውቋል፡፡ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት ውስጥም አንባብያን እጅ እንደሚደርስ አክሏል፡፡
በተመሳሳይ “የሕይወት ዕጥፋት” መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ በደራሲ ደሳለው አዳነ የተደረሰው “የሕይወት እጥፋት” መጽሐፍ ፍቅርና የህይወት መልከ ብዙ ገጽታዎችን አጉልቶ የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ መጽሐፉ በተለያዩ የመጽሐፍ ማከፋፈያ መደብሮች ውስጥ ይገኛል፡፡
ሙዚቃ
የድምፃዊት ፍቅርአዲስ ነቃጥበብ አዲስ አልበም ሊወጣ ነው፡፡ የድምፃዊት ፍቅርአዲስ አዲስ አልበም “ደህና ሰው” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን፤ አልበሙ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን ለመገናኛ ብዙሃን አሳውቃለች፡፡ ድምፃዊቷ አዲሱን አልበሟን ለማስተዋወቅ እና በይፋ ለህዝብ ለማድረስ የፊታችን ማክሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጠሮ ይዛለች፡፡ ፍቅርአዲስ በ2008 ዓ.ም ለመጨረሻ ጊዜ ለህዝብ ያደረሰችው “ምስክር” የተሰኘ አልበሟን እንደሆነ የሚታወስ ነው፡፡
በሌላ መረጃ፣ “ማስታወሻ” የተሠኘው የወጣቱ ድምፃዊ አዲስ ለገሠ የሙዚቃ አልበም በዛሬው ዕለት ይለቀቃል። በርካታ የሀገራችን የሙዚቃ ባለሙያዎችን ያሳተፈው ይህ አልበም፣ አዲስ ለገሠ የራሱን ቀለም እና አቀራረብ ያስተዋወቀበት ስራ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
“ማስታወሻ” 14 ዘፈኖችን ያካተተ አልበም ሲሆን በዜማና ግጥም ይልማ ገብረዓብ፣ ሞገስ ተካ፣ አብነት አጎናፍር፣ ቢንአሚር አህመድ፣ ዓለማየሁ ደመቀ፣ አንተነህ ወራሽ፣ እሱባለው ይታየው፣ ናትናኤል ግርማቸው፣ አስታወሰኝ ረጋሳ፣ እዮብ ዕድሉ፣ ዳዊት ተስፋዬ እና ራሱ አዲስ ለገሰም ተሳትፈውበታል። በሙዚቃ ቅንብሩ ደግሞ ሚካኤል ሃይሉ፣ ኪሩቤል ተስፋዬ፣ ብሩክ አፈወርቅ እና ኤርሚያስ ሞላ ተሳትፈዋል፡፡ የማስተሪንግ ስራው በኪሩቤል ተስፋዬ ተከናውኗል። አልበሙ ከ10፡00 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ ለገሰ ይፋዊ ዩትዩብ ቻናልና በሁሉም ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መተግበሪያዎች በኩል ለአድማጮች ይደርሳል፡፡ ድምፃዊ አዲስ ለገሰ ከዚህ በፊት ለህዝብ ባደረሳቸው “እንጆሪ”፣ “እንጃ”፣ “እወድሻለሁ” እና ከአንድ ወር በፊት በለቀቀው “እቱ” የተሰኙ ነጠላ ዜማዎቹ ይታወቃል፡፡
ሥዕል
የቡድን የግራፊክስ ጥበብ ዓውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተው እና የተለያዩ ሰዓሊያን ስራዎችን የያዘው የጥበብ ዓውደ ርዕይ በመታየት ላይ ይገኛል። በዚህ አውደ ርዕይ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡ ከያኒያን መካከል ታደሰ ባይሳ፣ ሚኪያስ ሰለሞን፣ ቤርሳቤህ አለማየሁ፣ ምህረት እሸቱ፣ ዳግማዊ ጸጋዬና ሱራፌል መክብብ ይገኙበታል፡፡ አውደ ርዕዩ እስከ ፊታችን ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ ሲሆን፣ እየታየ ያለው ደግሞ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል ውስጥ በሚገኘው የፈንድቃ የባህል ማዕከል ውስጥ ነው፡፡
በአብርሃም ገብሬ