የ4 ዓመት ህጻን ልጅ በማገት 5 ሚሊዮን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

You are currently viewing የ4 ዓመት ህጻን ልጅ በማገት 5 ሚሊዮን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN ነሃሴ 17/2017

የ4 ዓመት ህጻን ልጅ በማገት 5 ሚሊዮን ብር የጠየቁ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገለጸ።

የእገታ ወንጀሉ የተፈፀመው ነሐሴ 12 ቀን 2017 ዓ/ም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ቦታው ቀጠና አራት እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪ መታደል ታደሰ በቤት ሰራተኝነት ነሀሴ 2 ቀን 2017 ዓ/ም በአቶ መልካሙ ረዳቴ እና በወ/ሮ መሠረት አየለ ቤት በአራት ሺህ ብር የወር ደመወዝ ተስማምታ ከገባች በኋላ በ10ኛ ቀኗ የቀጣሪዎቿን የአራት አመት ህፃን ዮሴፍ መልካሙ የተባለውን ይዛ መሠወሯ ተገልጿል።

የህፃኑ ወላጆች ልጃቸው እንደጠፋ ለፖሊስ ካመለከቱ በኋላ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ የምርመራና ክትትል ቡድን በማደራጀት ጠንካራ የክትትል ስራ ያደርጋል።

በዚህም ተጠርጣሪ መታደል ታደሰ እና በወንጀሉ የሆነውን የተከሳሽ የትዳር አጋር የሆነውን መሠረት አየለ ከተባለ ግለሰብ ጋር በሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሀን ከተማ ጫጫ ክፍለ ከተማ ህፃኑን አግተው 5 ሚሊዮን ብር ካላስገባችሁ ልጃችሁን በሕይወት አታገኙትም በማለት ይደራደራሉ።

በዚህ መሃል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ከደብረ ብርሀን ከተማ ፖሊስ ጋር በመተባበር ሁለቱንም ተጠርጣሪዎች ነሀሴ 17 ቀን 2017 ዓ/ም በቁጥጥር ስር አውሏል።

ታግቶ የነበረው ህፃን ዮሴፍ መልካሙን ከነ ሙሉ ጤንነቱ ለወላጆቹ ያስረከበ ሲሆን በተጠርጣሪዎቹም ላይ ቀጣይ ምርመራ እየተደረገባቸው ይገኛል።

የህፃኑ ወላጅ አባት አቶ መልካሙ ረዳቴ እና እናት ወ/ሮ መሠረት አየለ ልጃቸው ከታገተባቸው ቀን ጀምሮ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሰንበቻውን ገልፀው፤ ልጃቸው በህይወት እንዲገኝ የረዳቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ እና ከጎናቸው ለነበሩ አካላት ሁሉ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ተጠርጣሪዋን ያለ በቂ ተያዥ በእምነት ብቻ ወደ ቤታቸው እንዳስገቧት የገለፁት የህፃኑ ቤተሰቦች ትክክል እንዳልነበሩም ተናግረዋል፤ ማንኛውም ሰው የቤት ሰራተኞችን ሲቀጥር በኛ የደረሰው እንዳይደርስበት በሕግ አግባብ መቅጠር ይኖርበታል ሲሉ መናገራቸዉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በላከዉ መረጃ አስታዉቋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review