በኢሉባቦር ዞን ከ500 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ አቮካዶ ለገበያ ለማቅረብ የምርት መሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነዉ

You are currently viewing በኢሉባቦር ዞን ከ500 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ አቮካዶ ለገበያ ለማቅረብ የምርት መሰብሰብ ስራ እየተሰራ ነዉ

AMN ነሐሴ 17/2017

በኢሉባቦር ዞን በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የተቀረጹ ኢኒሼቲቮችን ተከትሎ በተከናወኑ ተግባራት ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

በዞኑ ኢኒሼቲቩን ተከትሎ እየተከናወነ ባለ የፍራፍሬ ልማት የደረሰ የአቮካዶ ምርት የመሰብሰብ መርሃ ግብር ዛሬ ተከናውኗል።

በወቅቱም የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ቻላቸው አዱኛ እንደገለፁት፤ በፍራፍሬ ልማት ዘርፍ የተቀረጹ ኢኒሼቲቮችን ተከትሎ በዞኑ ሀስ (HASS) የተሰኘ ምርጥ የአቮካዶ ዝርያን በስፋት ማልማት መቻሉን ገልጸዋል።

በዞኑ ወረዳዎችም ከ7 ሺህ ሔክታር መሬት በላይ አቮካዶ ማልማት እንደተቻለና ከዚህም ከ500 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ አቮካዶ ለገበያ ለማቅረብ የምርት መሰብሰብ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይ ልማቱ በስፋት እየተከናወነባቸው ካሉ አካባቢዎች አንዱ የሆነው የበቾ ወረዳ አርሶ አደሮች ስራው የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ አቅምን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።

መንግስት የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ከሰጣቸውና በዞኑ እየተከናወኑ ከሚገኙ የግብርና መስኮች የፍራፍሬ ልማት ስራ አንዱ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ መሐመድ ጠሃ አባፊጣ ናቸው።

በዚህም አበረታች ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ገልፀው የፍራፍሬ ልማቱን በብዛትና በጥራት ለመከወን እየተሰራ ነው ብለዋል።

አቶ ኢማም አለሙ እና አቶ ከድር አህመድ የተባሉ የወረዳው አርሶ አደሮች በበኩላቸው በአቮካዶ ልማት በመሰማራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

በአሁኑ ወቅትም ለገበያ የሚያቀርቡትን የአቮካዶ ምርት በጥራት በመሰብሰብ ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review