የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጄ-ሚዩንግ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ወደ አሜሪካ አቅንተዋል፡፡
ሁለቱ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙ ሲሆን፣ በውይይታቸውም በንግድና በደህንነት ዙሪያ እንደሚመክሩ ተገልጿል፡፡
የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝዳንት ሊ ጄ-ሚዩንግ ከዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አሜሪካ በማቅናት የሚያደርጉት ውይይት፣ የአሜሪካንን እና የደቡብ ኮሪያን የቆየ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እና የቅርብ አጋር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተነግሯል፡፡
ሊ ከጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ ጋር በቶኪዮ የአንድ ቀን ቆይታ ካደረጉ በኋላ፣ እሁድ እለት በዋይት ሀውስ ከትራምፕ ጋር ለመወያየት ዋሽንግተን ዲሲ መግባታቸውንም መረጃው አመላክቷል።
ውይይቱ በተለይ ለደቡብ ኮሪያ ጠቃሚ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን ከዚህ በፊት ከአሜሪካ ጋር የነበራትን የፖለቲካ ግንኙነት ወደ ተሻለ ደረጃ ሊያሻሽለው ይችላል ተብሎ ታምኖበታል፡፡
ዉይይታቸዉ ደቡብ ኮሪያ በ100 ቢሊዮን ዶላር ከአሜሪካን ኢነርጂ ለመግዛት እና 350 ቢሊዮን ዶላር ደግሞ በአሜሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ ባለፈዉ ሃምሌ ወር የተስማማችበትን የንግድ ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ በሚያስችሉ ዝርዝር ተግባራት ላይ እንደሚያተኩሩ አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በአስማረ መኮንን