ግብርናን በማዘመን ረገድ በትኩረት ለመሥራት፣ የሜካናይዜሽን እርሻን ለማስፋፋትና የኩታ ገጠም አስተራረስ ስነ-ዘዴን በመጠቀም የግብዓት አቅርቦትን በተገቢ መልኩ ለማሳለጥ ትኩረት ይሰጣል ሲሉ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ ገልጸዋል፡፡
የሁሉም ክልሎች የግብርና ቢሮ አመራሮችና የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት በተገኙበት የተጠናቀቀው በጀት ዓመት የዘርፉ አፈፃፀም ግምገማና የ2018 ዓ.ም ዕቅድ የትኩረት አቅጣጫ ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የግብርና ሚኒስትሩ አቶ አዲሱ አረጋ፣ ከተረጂነት ለመላቀቅ የተጀመሩ ተግባራት በግብርና ዘርፍ ኢንሼቲቮች ተጨባጭ ውጤት እያመጡ ናቸው ብለዋል።
ለዚህም በበጋ መስኖ ስንዴ፣ በመኸርና በበልግ ሰብል ልማት፣ በቡና፣ በወተት ልማት እና በዓሣ ሀብት ልማት ከታቀደዉ በላይ ስኬት መመዝገቡን ገልጸዋል።
በመኸርና በበጋ መስኖ ስንዴ ላይ በተሰራው ስራ በየዓመቱ ከውጭ ይገባ የነበረውን ከ17 ሚሊየን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ማስቀረት መቻሉን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በቢራ ገብስ ላይ በተሰራው ስራ ከውጭ ይገባ የነበረውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት መቻሉን ሚኒስትሩ ገልፀው፣ ይህም ስራ ትልቅ ውጤት የተገኘበትና ዓለም አቀፍ ልምድ የተቀሰመበት መሆኑን አብራርተዋል።

በስንዴና በቢራ ገብስ ላይ የመጣውን ውጤት በሩዝ ላይ በመድገም ከውጭ የሚገባውን ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የተጀመረው ርብርብ ይጠናከራል ብለዋል።
ለዚህም በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌ፣ በአፋርና በሌሎች ክልሎች የተጀመሩ የሩዝ ልማት ስራዎች በቴክኖሎጂ በማስደገፍ ይበልጥ እንዲስፋፉ የማድረግ ስራ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ግብርናን በማዘመን ረገድ ትኩረት ተደርጎ እንደሚሰራ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ ለዚህም የሜካናይዜሽን እርሻን ማስፋፋትና የኩታ ገጠም አስተራረስ ስነ-ዘዴን በመጠቀም የግብዓት አቅርቦትን በተገቢ መልኩ ለማሳለጥ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል።
በዘርፉ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ አበረታች ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልፀው፣ በዘርፉ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ወጣቶችና ሴቶች በስፋት እንዲሳተፉ እንደሚሰራም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡