ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል እያበረከተች ያለው ሚና እና ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አንድምታ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል እያበረከተች ያለው ሚና እና ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አንድምታ

AMN – ነሐሴ 20/2017 ዓ.ም

ባለፉት በርካታ ቢሊዮን አመታት በዓለም የስነ- ምድር ታሪክ ውስጥ ብዙ ጊዜ የተከሰቱ የአየር ንብረት ለውጦች በጂኦግራፊያዊ እና በሥነ-ምህዳራዊ ስርዓቶች አማካኝነት እንደነበር በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡

በሌላ በኩልም በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ በተፈጥሯዊ ምክንያት የአየር ንብረት ለውጦች ተከስተው እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይሁን አንጂ ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሰዎች ተፅዕኖ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን በተለያዩ ጊዜአት የወጡ የጥናት ውጤቶች ያሳያሉ፡፡ በዓለም የኃይል ሚዛን ላይ በግልጽ እንደሚታየው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በርካታ አሉታዊ የሆኑ ውጤቶች እየተመዘቡ ይገኛሉ፡፡

በዚህም ምክንያት የምድራችን የሙቀት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ፣ በእያንዳንዱ ዜጋ ሕይወት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖዎች በማጋጠም ላይ ይገኛሉ፡፡ ለእነዚህ ውጤቶች መከሰት እንደ ምክንያት ከሚጠቀሱት ነገሮች መካካል የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፣ የደን ውድመት፣ እና መሰል ከአካባቢ ጥበቃ አያያዝ ማነስ ጋር የተያያዙ ችግሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡

ይህ ደግሞ የድርቅ መከሰት፤ የበረዶ መቅለጥና የውቅያኖሶች መጠን መጨመር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ከባድ ዝናብ መጣል፣ ከፍተኛ የሆነ የሰደድ እሳት እና ሌሎችም አደጋዎች እንዲከሰቱ ምክንያት እየሆነ መምጣቱን መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህ የአየር ንብረት ለውጥ መንስኤ ቀዳሚውን ደረጃ የሚይዙት በኢንዲስትሪ ያደጉና የበለፀጉ ሀገራት ቢሆንም፣ አነስተኛ አስተዋጽኦ ያላት አፍሪካም በሚደርሰው ተጽዕኖ ከፍተኛ ተጎጂ እየሆነች መምጣቷ በሰፊው ይነገራል፡፡

በመሆኑም ከዚህ ተፅዕኖ ለመላቀቅ የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 እንደ ዋነኛ ምሰሶ እና ግብ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል፡- ሁሉን አቀፍ እድገት እና ዘላቂ ልማት ላይ የተመሰረተ የበለፀገች አፍሪካ፣ ለአካባቢ ጥበቃ ዘላቂ እና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ እና ማህበረሰብ መገንባት እንደሆነ የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመላክታል፡፡ ይህን መሰረት በማድረግም የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የተለያዩ ስትራቴጂዎችን እና ግቦችን ነድፈው ወደ ስራ ገብተዋል፡፡

ኢትዮጵያም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከለከል የሚያስችል የራሷን ስትራቴጂና እና ግብ አስቀምጣ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች ትገኛለች፡፡ ለአብነትም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የታዳሽ ኃይል፣ የአረንጓዴ ትራንስፖርት፣ የፀሐይ፣ የነፋስ እና ሌሎች የኢነርጂ አማራጮችን መከተሏ እና መተግበሯ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በተለይም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከብክለት ነጻ የኃይል ምንጭ እንደሆነ እና ከራሷ ባለፈም ለምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከብክለት ነጻ የሆነ ኢነርጂ በማቅረብ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች፡፡ በዚህ የጎላ እንቅስቃሴዋም፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ስብሰባ ላይ ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባዔ እንድታዘጋጅ መመረጧ ይታወሳል፡፡

በዚህ ጉባኤም አፍሪካዊያን ለህልውና አስጊ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ በመወያየትና በመምከር ዘላቂ መፍትሄዎችን ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለይም የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር፣ በሃይል አቅርቦት፣ በሰብአዊ ልማት፣ በምግብ ዋስትና እና ብዝሃ ህይወት አጠባበቅን በተመለከተ በአጀንዳነት እንደሚዳስስ ይጠበቃል፡፡

ይህ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ፣ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እና በሰው ተኮር የልማት ስራዎች ላይ እያከናወነቻቸው የሚገኙ ስኬታማ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥርላት ታምኖበታል፡፡

በተለይም ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ለምታደረገው አበርክቶ ድጋፍ እና አጋር ለማግኘት እድል እንደሚፈጥርላት እና አጋጣሚውንም በበጎ መንገድ እንደምትጠቀምበት ይጠበቃል፡፡ ይህ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ፣ ከጳጉሜ 3 እስከ 5/2017 ዓ.ም ድረስ የአፍሪካ ዋና ከተማ በሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡

በአስማረ መኮንን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review