ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርዓት ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ርምጃ በመውሰድ ተጨባጭ ውጤቶች እያስመዘገበች መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በፓን አፍሪካ የአየር ንብረት ፍትህ ጥምረት የተዘጋጀው አምስተኛው የ2025 የአየር ንብረት ፍትህ የናይሮቢ የክረምት ትምህርት መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እየተካሄደ ነው። የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የናይሮቢ የአየር ንብረት ለውጥ የክረምት ትምህርትን ማዘጋጀቷ ታላቅ ኩራት ነው።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቀነስ የተለያዩ የፖሊስ ርምጃዎች በወሰደችበት እና ሁለተኛውን የአየር ንብረት ጉባኤ በምታስተናግድበት ወቅት በመሆኑ ክብር ይሰማናል ብለዋል።
መርሀ ግብሩ ከ141 የዓለም ሀገራት የተወጣጡ የአየር ንብረት ለውጥ ወጣት መሪዎች የታደሙበት መሆኑን በመጥቀስ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመከላከል ሚናቸው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።b የአየር ንብረት ለውጥ በየዓመቱ ከሁለት እስከ አምስት በመቶ ጥቅል የሀገር ውስጥ ምርት እንደሚያሳጣ በመግለፅ፣ በአፍሪካ ጉዳቱ የከፋ መሆኑን መጥቀሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ከአራት በመቶ የማይበልጥ ዝቅተኛ አስተዋፅኦ ቢኖራትም የጎላ ጉዳት እንደምታስተናግድ ገልጸዋል። በኢትዮጵያ በተለይም ዝቅተኛ በሆኑ አካባቢዎች ጎርፍና ድርቅ በሚልዮን የሚቆጠሩ አርብቶ አደሮችን የእንስሳት ሀብት ማሳጣቱን ተናግረዋል። በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አፍሪካውያን አፍሪካዊ መፍትሔ መፈለግ ይገባቸዋል ብለዋል።
በትብብር፣ ቁርጠኝነት፣ ፍትሐዊነት እና ተፈጥሮን መሰረት ባደረገ መፍትሄ የዓለም የአየር ንብረት ፋይናንስ ስርዓት እንዲስተካከል ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በሀገር በቀል የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስርዓት ተፈጥሮን መሰረት ያደረገ ርምጃ በመውሰድ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን አስታውቀዋል። በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር እንደ አውሮፓውያን የዘመን ቀመር በ2026 ላይ 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ እስከ አሁን 48 ቢሊዮን ችግኞች መትከሏን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ከፓሪስ ስምምነት ቀድማ ጉዳቱን በመገንዘብ ባከናወነችው ተግባር ውጤት ማምጣት መቻሏን ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ በአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት፣ በወንዝ ዳርቻዎች እና በስንዴ ልማት ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቧን ገልጸዋል።