ለሁለት አመት እንቅልፍ ያልተኛው ወጣት

You are currently viewing ለሁለት አመት እንቅልፍ ያልተኛው ወጣት

AMN – ነሃሴ 20/2017 ዓ.ም

ኦሊቨር አልቬስ የተባለው የ32 አመት ወጣት እንግሊዛዊ በባቡር አሽከርካሪነት ደስተኛ የሚባል ህይወት የሚመራ ሰው ነበር።

ከሁለት አመት በፊት በአንድ ምሽት ወደ ቤቱ ገብቶ እረፍት ለማድረግ ሲሞክር እንቅልፍ መተኛት ያቅተዋል ፣ ከዚህ ቀን ጀምሮ እንቅልፍን ለሁለት አመት ተሰናብቷል። ኦሊቨር ያለፉትን አመታት በእንቅልፍ ማጣት የተነሳ እያሳለፈ የሚገኘውን ስቃይ ሲገልጸው “በእሳት በሚቀጣጠል ሰው አካል ውስጥ እንደመኖር ነው” ይለዋል።

ወጣቱ ከዚህ ችግር ለመላቀቅ የተለያዩ የህክምና እርዳታዎችን ለማግኘት ገንዘቡን ቢያፈስም ማንኛውም ዶክተር ችግሩ ከምን እንደመነጨ ሊደርስበት አልቻለም። ህክምና ለማግኘት እያደረገ በሚገኘው ጥረት መኖሪያ ቤት እና ሌሎች ንብረቶቹን ሽጦ በአሁኑ ወቅት ከቤተሰቦቹ ጋር እየኖረ ይገኛል። ህንድ ፣ ጣሊያን ፣ ቱርክ እና ኮሎምቢያ ባህላዊ እንዲሁም ዘመናዊ ህክምናን ለማግኘት ተዘዋወረባቸው ሀገራት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት እጅግ በስቃይ የተሞላ ውሎ እና አዳርን እንደሚያሳልፍ የሚገልጸው ኦሊቨር ቀጥ ብሎ መራመድ እንደማይችል ፣ ሰውነቱን ለማንቀሳቀስ የሚቸገር ፣ የእይታ ብዥታ ፥ የአጥንት እና የመገጣጣሚያ ስፍራዎች ከፍተኛ ህመምን እና ሌሎች ስሜቶችን እንደሚያስተናግድ ለደይሊ ሜይል ተናግሯል።

“በጎዳና ላይ ሰላማዊ እንቅልፍን በሚተኙ ሰዎች እቀናለሁ ይህን ሰለማዊ እንቅልፍ ለማግኘት በእጄ ላይ የሚገኙ ንብረቶችን በሙሉ እለውጣለሁ” ሲል ወጣቱ በምን አይነት አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጿል። ከእንቅልፍ ማጣት ጋር በተያያዘ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉ ሀኪሞች እና ተመራማሪዎች እንዲረዱትም ተማጽኗል ።

ዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review