በራስ ጥረትና ፈጠራ እውቅና የተቸረው ባለዕራይ ትጋት

You are currently viewing በራስ ጥረትና ፈጠራ እውቅና የተቸረው ባለዕራይ ትጋት

AMN- ነሀሴ 21/2017

ከቤተሰብ ጋር የሚሰሩት ሥራ በፈጠራ የተሞላ ቢሆንም፣ አትራፊ ሆኖ በኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ አልሆን ስላላቸው ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት ይዘው ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ለመቀጠር መወሰናቸውን ያወሳሉ። አቶ ዮሐንስ ግርማ ይባላሉ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በብረታ ብረት ስራ ላይ ተሰማርተዉ በመስራት ላይ ይገኛሉ፡፡

በጥቂት መርጃ መሳሪያዎች እና በ5 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል የጀመሩት የብረታብረት ስራ፣ አሁን ላይ ተስፋፍቶ 50 ሚሊየን ብር ገደማ ደርሷል፡፡ አቶ ዮሐንስ ከተግባረ ዕድ የሙያ ማሰልጠኛ በኤሌክትሪክ ሙያ ተመርቀው የሜካኒካል ኢንጂነርንግ ሙያ ካላቸው አባታቸው ጋር በመስራት እንዴት አሁን ወደያዙት ሙያ እንደተሰማሩ ይገልፃሉ፡፡ ምንም እንኳን ከቤተሰብ ጋር የሚሰሩት ሥራ በፈጠራ የተሞላ ቢሆንም፣ አትራፊ ሆኖ በኢኮኖሚ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ አልሆን ስላላቸው ያካበቱትን ልምድና ዕውቀት ይዘው ሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ለመቀጠር መወሰናቸውን ያወሳሉ።

ይሁን እንጂ ሁሉም ነገር እንዳሰብኩት አላገኘሁትም የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ ተቀጥረው ለሥራ በገቡባቸው ድርጅቶች በርካታ ፈታኝ የህይወት ውጣ ውረዶችን እንዳሳለፉ ይናገራሉ። በስራቸው ለመለወጥ ትልቅ ዓላማ ቢኖራቸውም፣ ነገሮች አልጋ በአልጋ ሆኖ አልጠበቃቸውም፡፡ በዚህም ስራ እስከ መፍታት እና አስቸጋሪ ህይወት እስከ መምራት ደርሰዋል፤ ከዓመታት በፊት ግን ለህይወታቸው መቀየር መሠረት የጣለ አጋጣሚ ተፈጠረ።

በማህበር ተደራጅተው አብረዋቸው ለመስራት የተነሱ የሙያ አጋሮቻቸው፣ ለውጥን በአንድ ጊዜ ለማየት ከመሻትና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ኋላ በማፈግፈግ ከስራው መራቃቸውን የሚያነሱት አቶ ዮሐንስ፣ በጥቂት በጥቂት በማደግ ወዳሰቡት ከፍታ መድረስ ይቻላል በሚል አቋም በመጽናት ሥራቸውን ይቀጥላሉ። ከትንሽ የብረታ ብረት ሥራ የጀመሩትን ስራ በማስፋት፣ አሁን ላይ ከአዕምሮአዊ ንብረት የፈጠራ ባለቤትነት ዕውቅና ያገኙበትን የሽንኩርት መፍጫ ማሽን ጨምሮ፣ የተለያዩ ማሽኖችን በማምረት ከፍ ያለ ገቢ እና ዕውቅናን መጎናጸፍ ችለዋል።

የእርሳቸው የፈጠራ ውጤት የሆነው የሽንኩርት መፍጫ ማሽን፣ በሀገር ውስጥ በብዙ ስፍራዎች ተመራጭ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ ተጠቃሚዎች ማሽኑን ከሽንኩርት አልፈው ለተለያዩ ግልጋሎቶች እያዋሉት መሆኑን እንደነገሯቸው ያስረዳሉ። ፂዮን ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ፣ አሁን ላይ ከ20 በላይ ለሚሆኑ ቋሚ እና ከ20 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር የቻለ ችሏል፡፡ በዓመት በሚሊየን የሚቆጠር ገቢ በታማኝነት ለሀገር እያስገባ ይገኛል።

በኢትዮጵያ የተሰራ የሚሉ ምርቶችን ከሀገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ በሰፊው የማቅረብ ፍላጎት እንዳላቸው የሚገልጹት አቶ ዮሐንስ፣ ይህንን እውን ለማድረግ ማነቆ የሆኑ ተግዳሮቶች እንዲቀረፉላቸው ጠይቀዋል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review