የወጣቶችን ተስፋ ያለመለመው የዘመናችን አድዋ

You are currently viewing የወጣቶችን ተስፋ ያለመለመው የዘመናችን አድዋ

AMN – ነሃሴ 19/2017 ዓ.ም

ወጣቶች የአንዲት ሃገር የመጭው ጊዜ ተስፋ እና የለውጥ ሃይል ናቸው፡፡ ይህንን የለውጥ ሃይል የሆነውን ወጣት በተገቢው መንገድ ለልማት መጠቀም ከተቻለ ሃገርን የማሻገር ዓቅሙ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካላት የህዝብ ብዛት አንፃር የወጣቶች ቁጥር የላቀ ስለመሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ይሁን አንጂ ሃገሪቱ የቁጥሩን መጠን ያህል ተጠቃሚ ለምን አልሆነችም?

ታዲያ ይህንን የዘመናት ጥያቄ ለመመለስ፣ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፋፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ ተቀርፀው ወደ ስራ በመገባታቸው ወጣቶች የስራ ዕድል ተጠቃሚ እና የፈጠራ ስራ ላይ ተሳታፊ ሆነዋል፤ ውጤትም ተገኝቷል፡፡ በኢትዮጵያዊያን አንድነት እና ህብረት ከተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፡፡ ይህ ግድብ የዜጎች የዓመታት ቁጭት ውጤት ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ህዝቡ በነቂስ ደስታውን ከመግለፁ ባሻገር ሁሉም የቻለውን የገንዘብ፣ የሞራል እና የአይነት ድጋፍ በማድረግ ግንባታውን የደገፈበት፣ የትውልዱን ዳግማዊ አድዋን የሰራበትና አሻራውን ያሳረፈበት ፕሮጀክት ነው፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በተለይም ለኢትዮጵያዊያን ወጣቶች ልዩ ትርጉም ያለው ነው፡፡ኢትዮጵያን ከድህነት ለማውጣት ትልቅ ሚና ያለው ይህ ግድብ በወጣቱ ልብ ውስጥ የሚዘራው ተስፋ ምን ያህል ጥልቅ እንደሚሆን መገንዘብ አያዳግትም፡፡

ከግንባታው ሂደት ጀምሮ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል የፈጠረው የህዳሴው ግድብ ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ ደግሞ አዳዳዲስ ግዙፍ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡ በሥራ ላይ ያሉትም በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ በማስቻል በርካታ የሥራ ዕድሎችን ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል፡፡

ታዲያ አስራ አራት ዓመታትን የተጓዘው የግድቡ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ በቅርቡ ሊመረቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸው ይታወቃል ፡፡ ይህንን የአዲስ ዓመት ሙሽራ ለመቀበል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጉጉት እየተጠባበቀ ይገኛል፡፡

ውልደቷና ዕድገቷ እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ተስፋነሽ ሃይለማሪያም ትባላለች፡፡ የህይወት ምዕራፍ ሆነና ከዓመታት በፊት የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በስደት ከሃገር ወጥታ ታውቃለች፡፡ የስደት አስከፊነቱን እያስታወሰች ስደት ዓይኑ ይጥፋ የምትለው ተስፋነሽ ነገር ግን ስደትን በመርገም ብቻ ከድህነት መላቀቅ አይቻልም ነው ያለችን፡፡

በግብፅ ሃገር በስደት በነበረቸበት ጊዜ ከስደት ውጣ ውረዱ በላይ የሚያሳስባትና ሁሌም ቁጭት የሚፈጥርባት ታላቁ ወንዛችን የሆነውን ዓባይን ለዘመናት ሳንጠቀምበት የመኖራችን ጉዳይ ነው፡፡ በግብፅ ሃገር የሁሉም ነገር መሰረት ዓባይ መሆኑን ሳስብ እኛስ ከወንዙ መጠቀም እንዴት አቃተን የሚለው ጥያቄ ሁሌም ዕረፍት ይነሳኝ ነበር ስትል ያጫወተችን ፡፡

ታዲያ የሷና የመላው ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት የሆነው በዓባይ ወንዝ የመጠቀም ህልም እውን ሊሆን፤ መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡ ሲበሰር የፈጠረባት ስሜት ዛሬም ድረስ አትረሳውም ፡፡

ግድቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲውል የሚሰጠውን ጥቅም ሳስብ ያኔ ገና የአፍላነት እድሜዬን በስደት እንዳሳልፍ ምክንያት የሆነኝን ድህነትን አራግፈን በመጣል ለወጣቶች የተሻለ ዕድል ይፈጥራል፣ ይህም በሃገር ሰርቶ መለወጥ እንደሚቻል እና በአንድነት ተባብረን ከተነሳን የማንሰራው እና የማንፈፅመው ፕሮጀክት እንደማይኖር ያሳያል ስትል ትናገራለች፡፡

ደስ እያላትም የተጀመረውን ከድህነት የመውጫ መንገድ ለማገዝ እንደ አንድ ዜጋ ለግንባታው የቦንድ ግዥ መፈጸሟን አስታውሳናለች፡፡

እንደ ተስፋነሽ ሁሉ ያነጋገርናቸው ሌሎች ወጣቶችም፤ የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የአንድነት፣ የህብረት እና የቁርጠኝነት ውጤት ነው ብለዋል፡፡

እኛም እንደ ወጣትነታችን ቦንድ በመግዛት ተሳትፎ ስናደርግ ቆይተናል ያሉት ወጣቶቹ ግድቡ በቅርቡ እንደሚመረቅ ከመሪያችን አንደበት በሰማንበት ወቅት የተሰማን ደስታ ወደር አልነበረውም ሲሉ ገልፀዋል፡፡

ነገ በሃገር ሰርቶ ለመቀየር ያለንን ተስፋ ያለመለመ የዘመናችን አድዋ ነው ሲሉም ነው ወጣቶቹ ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል የተናገሩት፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review