በሳህል ቀጠና የምዕራባውያንን ተጽዕኖ የነጠቀችው ሩሲያ

You are currently viewing በሳህል ቀጠና የምዕራባውያንን ተጽዕኖ የነጠቀችው ሩሲያ

AMN – ነሃሴ 21/2017 ዓ.ም

ለአስርት አመታት በምዕራብ አፍሪካ ወታደሮቻቸውን አሰማርተው ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ምዕራባውያን በቀጠናው የፖለቲካ ቅርጽ መቀየሩን ተከትሎ ሳይወዱ በግድ ከአካባቢው እየለቀቁ ነው።

ከ2020 ጀምሮ 9 መፈንቅለ መንግስት የተካሄደበት የሳህል ቀጠና ከአሸባሪዎች ጋር እየተፋለመ ፖለቲካውን ለማረጋጋት ጥረት እያደረገ ይገኛል።

በዚህ ሂደት ውስጥ በአካባቢው ከተመሰረቱ ወታደራዊ መንግስታት ጋር ወዳጅነቷን ያጠናከረችው ሞስኮ በኢኮኖሚ እና በመሰረተ ልማት ግንባታ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ ወጥናለች።

እነዚህ እንቅስቃሴዎች ሞስኮን በአካባቢው የጂኦፖለቲካዊ የበላይነትን እንደሚያላብሳት የዘገበው ቢቢሲ፥ በአንጻሩ የሀገራቱን የቀድሞ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይን እንዳስቆጣ አስነብቧል።

ሩሲያ በዩራኒየም ማዕድን በበለጸገችው ኒጀር የኒውክሌር ሀይል ማመንጫ ለመገንባት የወሰደችው እርምጃ ፓሪስን ጨርሶ ከአካባቢው የሚያርቅ ነው።

የፈረንሳዩ የማዕድን ኩባንያ ኦራኖ በኒጀር የነበረውን የዩራኒየም ማውጫ ስፍራ በፕሬዝዳንት አብድሮህማን ቲቻኒ መንግስት ከተነጠቀ በኃላ ወደ ፈረንሳይ የሚላከው የብረት ጥሬ እቃ እንዲቋረጥም ተደርጓል።

በሩሲያ የኢነርጂ ድርጅት ሮዛቶም እና በኒጀር መንግስት በተፈረመው የትብብር ስምምነት መሰረት፣ ሩስያ ከምትገነባቸው የኒውክሌር ሀይል ማመንጫዎች ባለፈ የሀገሪቱን ባለሙያዎች በመድሀኒት እና በሀይል አማራጭ ምርምር ታሰለጥናለች።

ፕሮጀክቱ ተሳክቶ ወደ ትግበራ የሚገባ ከሆነ በምዕራብ አፍሪካ የመጀመሪያው የሀይል ማመንጫ ከመሆኑ ባሻገር፥ አብዛኛውን የሀይል ፍጆታዋን ከውጭ በምታስገባው ኤሌክትሪክ ለምትሸፍነው ኒጀር ጠቀሜታው ከፍ ያለ ነው።

ኦራኖ የተባለው የፈረንሳይ የኢነርጂ ኩባንያ ያቋቋማቸው የዩራኒየም ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በአሁኑ ወቅት በኒጀር መንግስት ቁጥጥር ስር ይገኛሉ።

ሞስኮ በነዚህ ፋብሪካዎች በከፊል የተቀነባበረ “የሎ ኬክ” በመባል የሚታወቀውን ዩራኒየም ከኒጀር ለመግዛትም ተስማምታለች።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review