ኢትዮጵያ አጋጥሟት የነበረውን የኢኮኖሚ ስብራት ለመጠገን ባለፉት የለውጥ አመታት መንግስት በልዩ ትኩረት ሰርቷል፡፡ ወደ ትግበራ ከገባ አንድ ዓመት የሞላው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ሀገሪቱ ካጋጠማት ስብራት አገግማ ለጀመረችው የብልፅግና ጉዞ መሰረት እንድትጥል አስችሏታል። ኢትዮጵያ በራሷ ገቢ ወጪዎቿን የምትሸፍንበት ደረጃ ላይ ማድረስ አንዱ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ገቢ የልማትና የዕድገት ሁሉ መሠረት ነው፤ የገቢ አቅማቸውን አሟጠው መጠቀም የቻሉ ሀገራት በልፀገው የመታየታቸው እውነትም ከዚሁ ይመነጫል።የአዲስ አበባ ከተማ የኢትዮጵያም የአፍሪካም ትልቋ መዲና እንደ መሆኗ መጠን ግዙፍ የልማት ሥራዎች ይከናወኑባታል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ከተማን መቀየር ለቻለው ልማት የዛሬው ትውልድ ህያው ምስክር ነው።
ታዲያ እነዚህ አዲስ አበባ ከተማን የቀየሩ ግዙፍ የልማት ሥራዎች የፋይናንስ አቅም የመፈለጋቸው ጉዳይ አያጠያይቅም። የፋይናንስ አቅም ከማንም ሳይሆን ከኢትዮጵያዊያን ታታሪ የሥራ እጆች የሚገኝ ነው፡፡ ለዚህም ቁርጠኛ መንግሥታዊ አስተዳደር ሥርዓትና ለልማት ቀናዒ የሆነ ታታሪ ህዝብ ያላት በመሆኑ ገቢን በሚገባ ሰብስባ ወደፊት ለመስፈንጠር ብርቱ ጥረት ላይ ትገኛለች።
ገቢን ፍትሀዊነት ባለው መልኩ መሰብሰብ ታዲያ ለመሰል የልማት ሥራዎች የጀርባ አጥንት ሆኖ ያገለግላል፡፡በአዲስ አበባ ከተማም ፍትሀዊነትን እና የገቢ አቅምን ለማሳደግ የገቢ ዘርፍ ሪፎርም ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል። ሪፎርሙ ውጤት ማስገኘቱን ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አገልጋይ ዝግጅት ጋር ቆይታ ያደረጉት የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢንያም ምክሩ ገልፀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ በራሷ ገቢ የምትተዳደር ከተማ መሆኗንም ተናግረዋል። ለከተማዋ ከፌደራል መንግስት የሚሰጥ ድጎማ አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡የግብር ፍትሀዊነት ሲባል ግብር ከፋዩ መክፈል የሚገባውን ብቻ መክፈል፣ የማይከፍል ካለ እንዲከፍል ማስቻል እንዲሁም የገቢ መሰረቶችን ማስፋት ነውም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በከተማ የተጨማሪ እሴት ታክስ(VAT) የመሰብሰብ አቅም ማደጉን ገልፀው፣ 14ሺ ሰዎችም ወደ ተጨማሪ እሴት ታክስ(VAT) ሥርዓት መግባታቸውን አስረድተዋል። ቀደም ሲል የደመወዝ ግብር የማይከፍሉ ከነበሩ በርካታ የግል ድርጅቶችም ታክስ መሰብሰብ ተችሏል ነው ያሉት ሃላፊው በቆይታቸው።
ይህ ፍትሀዊነትን የማረጋገጥ ሥራ አካል መሆኑን በማከል። ዕዳ የሚከታተል፣ የታክስ ውሳኔዎች ጥራት እና ብልሹ አሰራር የሚከላከል የሥራ ክፍል በአደረጃጀት ፀድቆ ወደ ሥራ ተገብቷልም ነው ያሉት። በተለይም በአፍሪካ ትልቁ የገበያ ማዕከልነቱ በሚታወቀው መርካቶ ላይ በህግ ማስከበር ሥራ የተሠራው ሥራ ውጤት ማስገኘቱን አስገንዝበዋል።
ይህንን ሥራ ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የሚያስችል መርካቶ አንድ እና መርካቶ ሁለት ላይ የነበረውን የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅ/ቤቶችን ሙሉ ለሙሉ ህግ የማስከበር ሥራ ብቻ የሚሰራባቸው እዲሆኑ ተደርጓል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የግብር ከፋዮችን ፋይል ወደ ግብር ሰብሳቢ ቅርንጫፎች መላኩን እና ለግብር ከፋዮችም በተለያዩ አማራጮች መረጃ መተላለፉን አቶ ቢንያም ተናግረዋል፡፡
ቢሮው ያካሄደው የገበያ ጥናት በ2017 ዓ.ም ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር ተያይዞ ትልቅ ገቢ እንዲሰበሰብ አስችሏል ብለዋል። በአግባቡ በሸጠበት ዋጋ ደረሰኝ የቆረጠ ነጋዴ ከዋጋ ጥናታችን ጋር አይጋጭምም ነው ያሉት። ነገር ግን የታክስ አስተዳደር ህግ በሚጥሱት ላይ እርምጃዎች መወሰዳቸው እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል።
በማሬ ቃጦ