አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያ በሆነው ፍጥነትን ማስተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የወርቅ ተሸላሚ ሆነች

You are currently viewing አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያ በሆነው ፍጥነትን ማስተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የወርቅ ተሸላሚ ሆነች

AMN – ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም

አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያ በሆነው ፍጥነትን ማሰተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር ላይ የወርቅ ተሸላሚ ሆነች፡፡

ብሉምበርግ ፍላንተሮፒስ በፍጥነት አስተዳደር ላይ ህጎችን በማውጣት እና ተግባራዊ በማድረግ የመንገድ ደህንነትን ያሻሻሉ ከተሞችን አወዳድሮ እውቅና ሰጥቷል፡፡

አዲስ አበባ በዓይነቱ የመጀመርያ በሆነው እና ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ዋሽንይግተን ዲሲ ከተማ ላይ ባዘጋጀው ፍጥነትን ማሰተዳደር ዓለም አቀፍ ውድድር የወርቅ ሽልማት አሸናፊ ሆናለች፡፡ አዲስ አበባ በመጨረሻ ለሽልማት ከታጩ ስምንት ከተሞች አንደኛ በመውጣት የወርቅ ተሸላሚ መሆኗ ይፋ ተደርጓል፡፡

ከ2015 እስከ 2017 በኢንሼቲቩ ውስጥ ያሉ ከተሞች እና አስተዳደሮች በዓለም ጤና ድርጅት (WHO) የሚመከሩ የፍጥነት ገደቦችን ወስደው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ ተደርጎላቸው የነበረ ሲሆን፤ ይኸውም አጠቃላይ የከተማ ውስጥ የፍጥነት ወሰን ስታንዳርድ በሰዓት ከ50 ኪሎ ሜትር በታች እንዲሁም በትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታሎች፣ ገበያ ቦታዎች እና ሌሎች ለትራፊክ ግጭት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ከ 30 ኪ.ሜ በሰዓት በታች በማድረግ በፍጥነት ማሽከርከርን መቀነስ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎችን ነድፎ ስራ ላይ ማዋል ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ብሉምበርግ ፍላንተሮፒስ ኢንሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ ባዘጋጀው የመንገድ ደህንነትን ማስተዳደር ላይ ከተማችን ባስመዘገበችው ተጨባጭ ውጤት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወርቅ ሽልማት አሸናፊ በመሆኗ ታላቅ ክብር ተሰምቶናል ብለዋል፡፡ እውቅናው ከተማችን ፍጥነትን ለማስተዳደር እና የመንገድ ደህንነት ለማሻሻል እየወሰደች ያለውን ጠንካራ ቁርጠኝነት ዳግም የሚያረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።

በሽልማቱ ያገኘነውን የ100 ሺህ ዶላር ሽልማት በቀጣይ የከተማዋ መንገዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ፣ ጤናማ እና ለነዋሪው ተስማሚ ምቹ አካታች እንዲሆኑ የሚያስችሉ የማሻሻያ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ እገዛ ያደርግልናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከተማዋ የፍጥነት አስተዳደርን በፈጠራ እና በአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች የታገዘ በማድረግ የተሻለ ለውጥ ለማምጣት እንደሚሰራ ቃል ገብተዋል፡፡

በተለይም ከተማ አቀፍ አውቶማቲክ የፍጥነት መቆጣጠሪያ ካሜራዎች እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ የትራንሰፖርት ስርዓት ተግባራዊ እንደሚደረግም ተገልጧል፡፡ እንደ ብሉምበርግ ገለጻ፣ ብሉምበርግ ኢኒሽዬቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ በዓለም ላይ ባሉ አገሮች ውስጥ ካሉ አጋር ድርጅቶች ጋር ሕይወትን ለማዳን ለሁለት አስርት ዓመታት ያህል በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኝ ከከንቲባ ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review