ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ መካከል የማዳበሪያ ማምረቻ ኮምፕሌክስ የድርሻ ስምምነት በዛሬው ዕለት መፈረሙን ይፋ አድርገዋል።
ይህን ተከትሎ የዳንጎቴ ግሩፕ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊኮ ዳንጎቴ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በማብራሪያቸውም፤ ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የሌላት እና ከውጪ ሀገራት በግዥ የምታስገባ መሆኗን አውስተዋል። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ከዓለም ግንባር ቀደም አምራቾች አንዷ የሚያደርጋትን ግዙፍ የአፈር ማዳበሪያ ማምረቻ ለመገንባት ዛሬ ስምምነት መፈረሟን አንስተዋል።
ይህን በዓመት ሦስት ሚሊየን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ የማምረት አቅም ያለው ፋብሪካ በተያዘለት ጊዜና ጥራት እንደሚያከናውኑም አረጋግጠዋል። የማዳበሪያ ፋብሪካው ኢትዮጵያ እየተጓዘችበት ላለው የብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት የግብርናውን ዘርፍ በአግባቡ በመደጎም ከፍተኛ ሚና እንደሚያበረክት ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል። ኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ የምታስገባ ገዥ ሳትሆን የራሷን ፍላጎት ከመሸፈን ተሻግራ ለሌሎች ሀገራት ላኪ እንደምትሆንም አስረድተዋል።
የአህጉራችን ኩራት እና የአፍሪካ ሕብረት መቀመጫ በሆነችው ኢትዮጵያ ቀደም ሲል በሲሚንቶ ማምረት ዘርፍ በኢንቨስትመንት መሳተፋቸውንም አውስተዋል። አሁን ደግሞ በማዳበሪያ ማምረቱ ሂደት ኢትዮጵያ በቂ ግብዓት ያለባት ሀገር መሆኗን አንስተው፤ ለዘርፉ ስኬታማነት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። የማምረት አቅሙ በዘርፉ ከፍተኛ አምራች ከሆነችው ናይጄሪያ ጋር ተመሳሳይ መሆኑንም አስረድተዋል።
ለሀገራቸው የሚያስፈልገውን ወቅቱን የዋጀ ሥራ እያከናወኑ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለራዕይ መሪ ናቸው ሲሉም ገልጸዋል። ይህ ሜጋ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ኢንቨስትመንት እንደሚፈስበትም ተመላክቷል።