የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካውን በአርባ ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካውን በአርባ ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN-ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና በዳንጎቴ ግሩፕ የሚገነባውን የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በአርባ ወራት ለማጠናቀቅ ይሰራል ሲሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ በ 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን አስመልክተው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራርያ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታውን በአርባ ወራት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

የዳንጎቴ ግሩፕ በአፍሪካ ደረጃ ትልቁ የማዳበርያ ፋብሪካ ያለው ተቋም መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ በኢትዮጵያም ላለፉት 16 ዓመታት የሲሚንቶ ፋብሪካ ላይ ኢንቨስት እያደረገ ያለ ተቋም መሆኑን አንስተዋል፡፡

የተደረሰው ስምምነትም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለግብርና ግብዓት የሚውል ዩሪያ የሚያመርት ፋብሪካ የመገንባት ነው ብለዋል፡፡

በዚህም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የ40 በመቶ ድርሻ ያለው መሆኑን የገለጹ ሲሆን የዳንጎቴ ግሩፕ ደግሞ የ60 በመቶ ድርሻ እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ያላትን የተፈጥሮ ነዳጅ በመጠቀም የነዳጅ ማስተላለፍያ መስመር ተገንብቶለት ወደ ስራ እንደሚገባም መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዳንጎቴ ግሩፕ መሰል ፋብሪካዎችን በመገንባት ልምድ ያለው ተቋም መሆኑን በማንሳት ይህንንም ፕሮጀክት በ40 ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ለዩሪያ ማዳበርያ አንደኛው ግብዓት የተፈጥሮ ነዳጅ ነው ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ይህንን ነዳጅ ከካሉብና ሂላላ ሪዘርቭ በመውሰድ ወደ 109 ኪሎሜትር የነዳጅ ማስተላለፍያ መስመር እንደሚገነባ ገልጸዋል፡፡

ይህ የነዳጅ ማስተላለፍያ መስመር ሶማሌ ክልል ጎዴ ድረስ የሚደርስ መሆኑን እና ፋብሪካውም በጎዴ የሚገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የተፈጥሮ ጋዙ ለሌሎች ግብዓት መሆን የሚችል በመሆኑ ከፋብሪካ በተጨማሪ በጎዴ የኢትዮጵያን የፔትሮኬሚካል ኢንዱስትሪ ለማቋቋም እቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review