የማዳበሪያ ፋብሪካው እንደ ሌላ ህዳሴ የሚታይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ

You are currently viewing የማዳበሪያ ፋብሪካው እንደ ሌላ ህዳሴ የሚታይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ
  • Post category:ልማት

AMN – ነሐሴ 22/2017 ዓ.ም

የማዳበሪያ ፋብሪካው እንደ ሌላ ህዳሴ የሚታይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በሁለት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ዶላር ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ ፕሮጀክት ግንባታ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህዳሴውን በጨረስንበት በዚህ ሰዓት የማዳበሪያ ፋብሪካውንና ሌሎች መጪ የኢትዮጵያን አቅም የሚያጎለብቱ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸው ሜጋ ፕሮጀክቶችን በሚቀጥሉት አምስት እና ስድስት ዓመታት እንጨርሳለን ብለዋል፡፡

ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚመጡት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም ሁልጊዜም እንደምንለው እና እንደምንመኘው የኢትዮጵያ ብልፅግና በአስተማማኝ መሰረት ላይ እንዲቀመጥ ያስችላል ብለዋል።

ከዛም ባለፈ ለሌሎች የአፍሪካ ወንድሞቻችን ፈር ቀዳጅ ሆኖ ብዙዎች እኛን ተከትለው አፍሪካ የምትለምን፣ የምትራብ እና ምትሰደድ ሳትሆን ራሷን የምታለማ፣ ራሷን የምትመግብና ለሌሎች የምትተርፍ የነገዋ አህጉር እንድትሆን በከፍተኛ ደረጃ ፈር የሚቀድ ጉዳይ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም መሰል ስተራቴጂክ ኢንቨስትመንቶችን እየለዩ በጥንቃቄ እና በጥናት ላይ ተመስርቶ መጀመር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የማዳበሪያ ፋብሪካው እንደ ሌላ ህዳሴ የሚታይ ነውም ብለዋል፡፡

በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሚመራውን ይህን ፕሮጀክት በተባለው ጊዜ እንደምንጨርሰውና ትሩፋቱንም በጋራ የምናይ እንደሚሆን ለማረጋገጥ እወዳለሁ ብለዋል።

በሚቀጥሉት 40 ወራት ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ላይ የሚጨበጥ ለውጥ አምጥቶ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጥረት የሚደግፍ መልካም ጅምር ነው ብለዋል።

በሊያት ካሳሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review