ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ የግንባታ ስምምነት ላይ ያተኮረ የዘገባ ሽፋን ሠጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ እና ዳንጎቴ ግሩፕ በ2.5 ቢሊዮን ዶላር የማዳበሪ ፋብሪካውን ለመገንባት ስምምነት ማድረጋቸው ይታወቃል፡፡
የግዙፉን ፕሮጀክት ስምምነት ተከትሎም ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ዘግበዋል፡፡
ፋብሪካው አፍሪካዊው ቢሊየነር አሊኮ ዳንጎቴ አፍሪካ ከውጭ የምታስገባውን ማዳበሪያ ለማስቆም የሚያደርጉት ጥረት አካል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በ X ገፃቸው ላይ መግለፃቸውን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል፡፡
ቲ አር ቲ በበኩሉ ይህ ስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ኢትዮጵን ከትላላቅ የማዳበሪያ አምራች ሀገራት ተርታ የሚያሰልፍ መሆኑን አንስቷል፡፡
ፋብሪካው ሲጠናቀቅ በዓመት 3 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ እንደሚያመርት መገለፁን በዘገባቸው የጠቆሙት መገናኛ ብዙሀኑ በዓመት 6 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ከውጭ ለምታስገባዋ የአፍሪካ አህጉር ትልቅ ትርጉም ያለው ሥራ መሆኑን አትተዋል፡፡
በማዳበሪያ እጥረት ምክንያት ለተቸገሩ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች እፎይታን ከመፍጠርም አልፎ የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ጉዞ ከግብ ለማድረስ አይነተኛ ሚና እንደሚያበረክት እንዲሁም ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር የውጭ መገናኛ ብዙሃኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ንግግር ጠቅሰው የዘገባቸው አካል አድርገዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለማዳበሪያ ፋብሪካ በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር በየዓመቱ ወጪ ታደርጋለች፣ ዛሬ ይፋ የተደረገው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ከዚህ ወጪ ይታደጋል ሲል ያስነበበው ደግሞ የናይጀሪው የበይነ መረብ መረጃ ምንጭ የሆነው ኔሮትሪክስ ነው፡፡
ይህ ለኢትዮጵያ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ማንሰራራት ሁነኛ ፕሮጀክት መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው ሀገራዊ ምርትን ከማሳደጉም በላይ ኢትዮጵያን ከውጭ ምንዛሬ ጫና ይታደጋታልም ብሏል፡፡
በ10 የአፍሪካ ሀገራት የሲሚንቶ ንግድ ሰንሰለት የዘረጋው ባለሀብቱ አሊኮ ዳንጎቴ ተመሳሳይ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገሩ ናይጀሪያ እየገነባ ይገኛል፡፡
ከቢሊየነሩ ዳንጎቴ ጋር በኢትዮጵያ ለሚገነባው የማዳበሪያ ፋብሪካ የውል ስምምነት መፈፀሙ በተለይም ፓን አፍሪካዊነትን ለማስፋፋት ጥንካሬ እንደሚፈጥርለት በዘገባው ተመላክቷል፡፡
ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር ያደረግነው ስምምነት አፍሪካን ወደ ኢንዱስትሪ ለማሻገር እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በጋራ ለያዝነው ራዕይ ይህ ወሳኝ ጊዜ ነው ሲሉ ዳንጎቴ መናገራቸውም ተጠቅሷል፡፡
በናይጄሪያ ከሶስት ዓመታት በፊት የተጀመረው እና በኢትዮጵያም የሚገነባው ትልቅ ፋይናንስ የሚጠይቀው የማዳበሪያ ፋብሪካ አፍሪካ ከድህነት ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነት አመላካች ሆኗል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፋብሪካውን ግንባታ አስመልክተው ታሪካዊ ጉዞ ጀምረናል፤ ለገበሬዎቻችን፣ ለኢኮኖሚያችን እና ለኢትዮጵያ ነገ ስንል እንጨርሰዋለን ሲሉ መግለፃቸውም ይታወሳል፡፡
በማሬ ቃጦ