አዲስ አበባ በዲኘሎማቶች አንደበት

You are currently viewing አዲስ አበባ በዲኘሎማቶች አንደበት

AMN – ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም

‎የአፍሪካ መናገሻ፣ የአለም የዲፕሎማቶች መናኸሪያ፣ የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ምሳሌ ሀገር መዲና፣ የበርካታ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሀይማኖታዊ መስህብ ባለቤት – አዲስ አበባ። የከተሞች አውራ የሆነችው የኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ለዘመናት የማይመጥኗት መሰረተ ልማት ተሸክማ ዘልቃለች። በውስጧ ያጨቀችው ጉድፍ ለአላፊ አግዳሚው ምቾት ሲነሳ ቆይቷል።

‎ይሁንና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የነበራትን ስም የቀየሩ በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፤ የከተማ ውበትና ጽዳት እንዲሁም ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በስፋት ማከናወን ጀምራለች፤ በዚህም አመርቂ ውጤት እየታየ ነው፡፡ አዲስ አበባ ባልተጠበቀ ፍጥነት ለሀገሬው ብቻ ሳይሆን ለሌላው ዜጋ የሚያስገርም ለውጥ እያስተናገደች መሆኑን ያያት ሁሉ ይመሰክራል፡፡ ስሟን የሚመጥን ልማት መስራት የዘውትር ተግባሯ ማድረግን ተያይዘዋልች።

‎በከተማዋ የሚገኙ ታሪካዊ ቦታዎችን ደረጃቸውንና ታሪካዊ ይዘቶችን ጠብቆ የለማበት መንገድ ለሌሎች ሀገራት አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ አዲስ አበባን የጎበኙ የ 41ኛው የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ጉባኤ ተሳታፊዎች ተናግረዋል። መዲናዋ ያለችበትን የእድገት ፍጥነት አዲስ አበባን የጎበኙ አፍሪካውያን እና የሌሎች አገሮች ዜጎች ይህንን እውነታ ይመሰክራሉ። ‎ከናምቢያ የመጡት ክሌመንቲና ካራሊስ ስለ መዲናዋ ሲያስረዱ፣ በአዲስ አበባ ባየሁት ለውጥ ምክንያት አፍሪካዊ በመሆኔ ኮርቻለሁ ብለዋል።

‎አዲስ አበባ ላይ መንግስት እየሰራ ያለው ስራ አስገርሞኛል ያሉት ጎብኝዋ፤ ይህም መንግስት ከህዝቡ የሚሰበስበውን ሀብት በአግባቡ ልማት ላይ እያዋለ እንደሚገኝ የሚያሣይ ነው ብለዋል ። የመዲናዋን የለውጥ ግስጋሴን ሲገልፁም፣ አዲስ አበባ ቀጣይዋ “የአፍሪካ ዱባይ” በማለትም የከተማዋን እድገትና ውበት አድንቀዋል። ከናይጄሪያ የመጣው ወጣት አቡበከር አብዱላሂ በበኩሉ የከተማዋ ውበትና እድገት በሚያስደንቅ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

‎የተደራጀች እና ውበ መሰረተ ልማቶች የተሟሉላት እንደሆነች ወጣቱ ገልፀው፤ ባዩት ነገር ሁሉ መደሰታቸውንና አድናቆታቸውን ችረዋል። ባየኋቸው ውብ ህንጻዎች ፣ማራኪ የህንፃ ጥበብ በጣም ተገርሜያለሁ ያሉት ደግሞ ከእንግሊዝ ሀገር የመጡት ታይለር ኢዝመን ናቸው። በአዲስ አበባ የተሠሩት የኮሪደር ልማቶች ተያያዥነት ያላቸው እና አንዱ ለአንዱ ተመጋጋቢና እንዲጣጣም ተደርጐ በመሰራቱ ከተማዋ የበለጠ ስሟን የሚመጥን እንዳደረጋት ይገልፃሉ። በተለይም ከተማዋን ምቹ እና ውብ ያደረጓት እነዚህ የመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች የተለያዩ አለም አቀፍ ጉባኤዎችን ለማዘጋጀት ተመራጭ ከተማ ያደርጓታል ብለዋል።

‎አዲስ አበባ ውብ ከተማ ሆናለች፤ መሰረተ ልማቶቿም አንዱ ከአንዱ ጋር የተጣጣሙ ሆነዋል ያሉት ደግሞ ከደቡብ አፍሪካ የመጡት ሞርዝስ ባዲቴሌ ናቸው። ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀትን ያላበሱት የመንገድ መብራቶቹን ያደነቁት ደቡብ አፍርካዊው፤ አዲስ አበባ በአጭር ጊዜ እንዲህ ውብ ትሆናለች ብዬ አልጠበኩም ብለዋል። ማማቲመላ ባኮቤላ ዶ/ር ከሀገረ ሌሴቶ ከመጡቱ መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ መዲናዋ ከተለያዩ አገሮች የመጡ እንደኛ አይነት እንግዶች የሚጎበኙት በርከት ያሉ ቦታዎች አሏት ብለዋል። በማስከተልም ይህ ሁኔታ በርከት ያሉ አለም አቀፍ መድረኮችን ለማስተናገድ ተመራጭ ያደርጋታል ሲሉ የሌሴቶዋ ጎብኚ ይናገራሉ።

‎የመንግሥት እና ህዝብ በጋራ የመቆም ውጤት ያመጣው ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የሚነገረው የአዲስ አበባ ልማት፤ ይህንን እውነት ጎብኚዎቿም ይጋሩታል። የአዲስ አበባ ውበት የመንግስትና የህዝብ የጋራ ትብብር ውጤት ማሳያ ነው ያሉት ጎብኚዎቹ፤ ለዚህ እውነት ማረጋገጫው በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከተማዋ መቀየሯ ነው ብለዋል። ይህንን አዎንታዊ ልምድ በሀገራችው ለመተግበር ስለማለማቸውም ነው ጎብኚዎቹ የሚገልፁት።

‎ከዚህ ሁሉ ልማት ጀርባ ጠንካራ የሆነ የመንግስት አካላት እንዳሉ ተገንዝቤያለሁ ያሉት ደግሞ ሌላኛው ኔዘርላንዳዊ ጉብኚ አርኖልድ ብራውን ናቸው። ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች አስተባብሮ በአንድ ላይ እንዲቆሙ ማድረግ ቀላል ስራ አይደለም ያሉት ጎብኚው፣ በጋራ ሰርቶ በጋራ መኖርን አይቼበታለሁ ሲሉ ተናግረዋል። ከከተማዋ ውበት የተረዳነውን የመንግስትና ህዝብ አንድነት ፣ተባብሮ ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ የሚያደርጉትን ጥረት ወደ ሀገራችን ለተሞክሮ እንወስደዋለን ሲሉ ደቡብ አፍሪካዊ ኢንታሻና ፖሻለን ተናግረዋል።

‎ታሪካዊ ቦታዎች ደረጃውን በጠበቀ መንገድ የተሰሩበትን ሁኔታ ለሌሎችም አገሮች አርአያ የሚሆን ስራ መሆኑን አመላክተዋል። ‎ኢትዮጵያ በቅኝ ግዛት ያልተገዛች አገር ናት፤ በርካታ ሀይማኖቶች የሚገኙባት መሆኗን እና ይህንን ታሪካዊ እውነታ በሰነዱበት መንገድ መገረማቸውን አስረድተዋል። አንድነት ፖርክን ስጎበኝ ተገርሜያለሁ፤ የተሰሩበት መንገድ እና ታሪኮቹ ያሉበት ይዞታ አስደንቆኛል ሲሉ ኔዘርላዳዊዉ ኪኩ ጊተርን ገልፀዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review