ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ለማሰባሰብ ለሚያከናውነው ተግባር አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ አገልግሎት ገልጿል።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመወያየት የአጀንዳ ማሰባሰብ ተግባር መጀመሩ ይታወቃል።
ኮሚሽኑ ደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ መረከቡ የሚታወቅ ሲሆን፤ በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ እና በካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫ ለማካሄድ የኮሚሽኑን ልዑክ ወደ ቦታው መላኩም ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ እንዳሉት፤ ሀገራዊ ምክክር በንግግር ተግባቦት በመፍጠር በጋራ አገርን ለመገንባት ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ምክክሩ በሃሳብ ልዩነት ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ቃላትን ከመወራወር ይልቅ በውይይት ለመፍታት እድል የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻሉ።
ኮሚሽኑ ከአሁን ቀደም በአገር ውስጥ በተለያዩ ክልሎችና ተቋማት ውይይቶችን በማካሄድ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ ከመስራቱ ባለፈ አሁን ላይ ከኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር ውይይት ማድረግ መጀመሩን አንስተዋል።
አገልግሎቱ ኮሚሽኑ ጋር ውይይት ከመጀመሩ በፊት ከኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን፣ ከሚሲዮን መሪዎችና ዲፕሎማቶች ጋር የተለያዩ የዝግጅት ውይይቶችን በበይነ መረብ ማካሄዱን አንስተዋል።
ኮሚሽኑ በደቡብ አፍሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አጀንዳ ማሰባሰቡን አስታውሰው፤ በሰሜን አሜሪካ፣ ካናዳ እንዲሁም ሌሎች ቦታዎች ለሚደረጉ ውይይቶች ከኤምባሲዎች ጋር በመነጋገር ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለማግኘት በሚፈልግበት ወቅት አገልግሎቱ ከኤምባሲዎች ጋር ትስስር በመፍጠር፣ጥሪ ከማድረግ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል።