የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰማሩ የባህር ላይ ዳርቻዎች ጥበቃ (costal guard) የፖሊስ ምልምል አባሎችን በመሰረታዊ ባህርተኝነት አሰልጥኖ አስመርቋል።
በባቦጋያ ማሪታይም እና ሎጂስቲክስ አካዳሚ በተካሄደው መርሀ ግብር የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የሰራዊቱ እና የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ስልጠናው በፌዴራል ፖሊስ ውስጥ አዲስ አደረጃጀትን የፈጠረ ነው። ስልጠናው በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሰረት መከናወኑንም ገልጸዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑን አመልክተው፤ በለውጡ መንግስት አማካኝነት ግድቡን ከነበረበት ውድቀት ማዳን መቻሉን ገልጸዋል። የፌዴራል ፖሊስ እና የሀገር መከላከያ ሰራዊት ግድቡን ከጅማሮው አንስቶ ሲጠብቁ መቆየታቸውን ጠቁመዋል። የፌዴራል ፖሊስ ኢትዮጵያ እያስመዘገበቻቸው ላሉ ስኬቶች የራሱን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አመላክተዋል።

በተጨማሪም እራሱን በቴክኖሎጂ በማብቃት በዓለም ደረጃ ትልቅ ክብርና አድናቆት የተቸረው ተቋም መሆኑን አንስተዋል። የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሰልጣኞችን በማብቃት ላበረከተው አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
የባህር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ስራ አስፈጻሚ በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድርጅቱ ለሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም በአካዳሚው በኩልም ባህርተኞችን ለዓለም ገበያ እያበቃ እያሰማራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያ በሁሉም መስክ እያንሰራራች መሆኑን ገልጸው፤ ይህንንም ማንም ወደኋላ የሚመልሰው አይደለም ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ስልጠናው ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የባቦጋያ ማሪታይም እና ሎጂስቲክስ አካዳሚ ዲን ሲራጅ አብዱላሂ ናቸው። ስልጠናው ዘመኑን የዋጀ ዓለም አቀፍ ይዘቱን የጠበቀ መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም ሰልጣኞች አስፈላጊውን እውቀትና ባህሪ መታጠቃቸውን ተናግረዋል። በመርሀ ግብሩ ለስልጠናው መሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ እና በስልጠናው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ እውቅና ተሰጥቷል።