ኢሰብዓዊ ተግባር በመፈፀም ሙያዊ ሃላፊነታቸውን ያጓደሉ የፖሊስ አባላትን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው የሚገኙት ምክትል ሳጅን አሸብር ግምጃው እና ረዳት ሳጅን ናትናኤል በላይ የተባሉ የልደታ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አባላት ናቸዉ፡፡
እነዚህ የፖሊስ አባላት ነሃሴ 21 ቀን 2017 ዓ/ም መደበኛ ስራቸውን እያከናወኑ በነበረበት ወቅት በግምት ከቀኑ 10 ሠዓት ገደማ ባልቻ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ተሽከርካሪ ውስጥ ተቀምጠው ጫት ሲቅሙ እና አደንዛዥ ዕፅ ሲጠቀሙ የነበሩ ግለሰቦችን አግኝተው በቁጥጥር ስር ለማዋል ባደረጉት እንቅስቃሴ ድርጊቱ ሊፈፀም ችሏል፡፡

በወቅቱ ጫት ከሚቅሙት ግለሰቦች ጋር አብሮ የነበረው የአብስራ ሳሙኤል የተባለው የግል ተበዳይ ከስፍራው ለማምለጥ በማሰብ ሲሮጥ የፖሊስ አባላቱ ተከታትለው የያዙት ቢሆንም መሬት ላይ እየጎተቱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ለመውሰድ የሞከሩበት መንገድ ግን ከሙያዊ ኃላፊነት ያፈነገጠ እና የሰብአዊ መብት አጠባበቅ መርህን ያልተከተለ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ አረጋግጧል፡፡
ሁለቱ የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ያስታወቀው ጠቅላይ መምሪያው፤ የፖሊስ አመራርና አባላት የተጣለባቸውን ሙያዊ ኃላፊነት ሲወጡ የሰዎችን ሰብዓዊ መብት ባከበረ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አሳስቧል፡፡
በስነ ምግባር ጥሰት ውስጥ በሚገኙ ፖሊሶች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ለኤኤምኤን በላከዉ መረጃ አስታዉቋል፡፡