መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም መሠረቱ የተጣለው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ እነሆ የምርቃቱ ሪቫን ሊቆረጥ ቀኑ ተቃርቧል፡፡ ለግድቡ መገንባት ህፃን፣ አዋቂ፣ ወንድ፣ ሴት ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በየአቅሙ ተረባርቧል፡፡ በዓለም ገና ከተማ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አስካለ በቀለ፤ ለግድቡ ግንባታ የአቅማቸውን አስተዋፅዖ ሲያደርጉ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን አንዷ ናቸው፡፡
የግድቡ ግንባታ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አሥራ አራቱንም ዓመታት ቦንድ በመግዛት በደስታ በአቅማቸው ሲሳተፉ ቆይተዋል፡፡ ከሚያገኙት አነስተኛ ወርሃዊ ደሞዝ እስከ አምስት ሺህ ብር የሚደርስ የቦንድ ግዢ የፈጸሙ ሲሆን፣ ግድቡ ሳይመረቅ የቦንድ ክፍያቸውን ላለመውሰድ መወሰናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ልጆቻቸውም የ10 እና የ6 ዓመት ሳሉ ጀምሮ በተደጋጋሚ በስማቸው ቦንድ ይገዙላቸው እንደነበር የሚገልጹት ወ/ሮ አስካለ፣ አሁን ላይ አንደኛው ልጃቸው ከዩኒቨርሲቲ እንደተመረቀና ሌላኛውም የ7ኛ ዓመት የህክምና ተማሪ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ተገንብቶ ለአገልግሎት ሲበቃ ማየት በጉጉት የሚጠብቁት ህልማቸው እንደሆነ የሚያነሱት እኚህ እናት፣ ከልጃቸው ጋር በተመሳሳይ ዓመት ሊመረቅ መሆኑም ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

ለዓባይ ወንዝ እና ለህዳሴው ግድብ ያላቸው ፍቅር ጥልቅ እንደሆነ በመግለፅም፣ ይህ ስሜት የተፈጠረባቸውም ለትምህርት ኩባ ሀገር በነበሩበት ወቅት ባጋጠማቸው ክስተት እንደሆነ ያነሳሉ፡፡
ትምህርት ቤታቸው ውስጥ የዓባይን ወንዝ የግብፅ አካል አድርጎ የሚያሳይ ምስል ተለጥፎ ያየ የትምህርት ባልደረባቸው፣ እንዴት ይሆናል በሚል ተከራክሮ ምስሉን ሲያስነሳና የለጠፈችውን ግብፃዊት ተማሪም ሲያስቀጣ ካዩ በኋላ እንደበር ያወሳሉ፡፡ ወደ ሀገራቸው ከተመለሱም በኋላ በሰለጠኑበት ሙያ ሀገራቸውን እያገለገሉ የሚገኙ ሲሆን፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ሲቀመጥ ልዩ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡
ከዛን ጊዜ ጀምሮም በግላቸው ቦንድ ከመግዛት ጀምሮ፣ ሌሎችን በማስተባበር ጭምር ከፍተኛ ተሳትፎ እያደረጉ ስለመቆየታቸው ገልጸዋል፡፡ ሰው እንደነዚህ ዓይነት አስተዋፅዖ ከተረፈው ሳይሆን፣ ካለው ላይ ነው ማድረግ የሚገባው የሚሉት ወ/ሮ አስካለ፣ ህብረተሰቡ ሀገራዊ ፋይዳ ላላቸው ይህን መሰል ፕሮጀክቶች የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክርም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በታምራት ቢሻው