የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ10ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች እያስመረቀ ነው።
በመከላከያ ሚኒስቴር በሰላም ማስከበር ማዕከል የሁርሶ ኮንቲንጀንት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለ10ኛ ዙር ያሰለጠናቸውን ምልምል ወታደሮች የሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮችና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በማስመረቅ ላይ ይገኛል።
የትምህርት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ ሌተናል ኮሎኔል በላይ ህሩይ እንደገለጹት፤ ትምህርት ቤቱ የላቀ ወታደራዊ እውቀትና ብቃት ያላቸውን ወታደሮች ማፍራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለሀገር ሉአላዊነት አስተማማኝ መከታ በመሆን የሚያገለግሉ እና እያገለገሉ ያሉ ጀግኖችን የሚያፈራ ተቋም መሆኑንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በዛሬው እለትም ለ10ኛ ጊዜ የሚመረቁት ምልምል ወታደሮች የላቀ ወታደራዊ ሳይንስ የተማሩና አስተማማኝ ብቃት ያላቸው መሆናቸውን ገልጸዋል። የትኛውንም ግዳጅ በብቃትና በጀግንነት መወጣት የሚያስችላቸውን የተግባርና የንድፈ ሃሳብ ስልጠና አግኝተው ለምረቃ የበቁ መሆኑንም ተናግረዋል።
በምርቃ ስነ ስርአቱ ላይ በመከላከያ ሚኒስቴር የሰው ሃብት ዋና መምሪያ ኃላፊ ሌተናል ጀነራል ሃጫሉ ሸለመ፣ የመከላከያ ሰላም ማስከበር ኃላፊ ሜጀር ጀነራል አዳምነህ መንግስቴ እና ሌሎችም የመከላከያ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና መኮንኖች ተገኝተዋል።