ስኬታማዎቹ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ሀገራት

You are currently viewing ስኬታማዎቹ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ሀገራት

የጤና ቱሪዝም ታካሚዎች ፈጣን፣ ዘመናዊ እና በተመጣጣኝ ዋጋ የሚገኝ የሕክምና አገልግሎት ፍለጋ ከሀገራቸው ውጪ ወደ ሌላ ሀገር የሚጓዙበት ሂደት ነው። ይህ ኢንዱስትሪ በዓለማችን እያደገ ያለ ሲሆን፣ ብዙ ሀገራት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ አድርገው እንደሚጠቀሙበት የጤና ቱሪዝም ማህበር (Medical Tourism Association) እ.ኤ.አ በ2023 ያወጣው መረጃ ያመላክታል፡፡

በዚህ መረጃ መሠረት፣ በዓለም ላይ የጤና ቱሪዝም ታዋቂ መዳረሻ ከሆኑ ሀገራት መካከል ህንድ፣ ቱርክ፣ ታይላንድ፣ ማሌዢያ፣ አሜሪካ፣ ደቡብ አሜሪካ እና የካሪቢያን ሀገራት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። በዚህ አምድም እነዚህን ሀገራት ዋቢ አድርገን በዓለም ላይ የጤና ቱሪዝም ዘርፍ የደረሰበት ደረጃ፣ በዘርፉ ስመጥር የሆኑ ሀገራት ተሞክሮና ተጠቃሚነታቸውን እንፈትሻለን፡፡ 

በየዓመቱ እስከ 14 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ለህክምና ወደ ሌሎች ሀገራት እንደሚጓዙ እ.ኤ.አ በ2024 የወጣው የዓለም የጤና ቱሪዝም ማህበር መረጃ ያሳያል፡፡ የጤና ቱሪዝም ለብዙ ሀገራት ከፍተኛ የገቢ ምንጭ እየሆነ መጥቷል። ይሁን እንጂ ሀገራት የሚያገኙት ገቢ እንደየሀገራቱ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ ዋጋ፣ የሚሰጡት የህክምና አይነቶች ሊለያይ ይችላል። የዓለም አቀፉ የህክምና ቱሪዝም ገበያ በየዓመቱ በአማካኝ በ8 ነጥብ 8 ቢሊዮን ዶላር እያደገ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2024 የገበያው ግምት ከ 41 ነጥብ 7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ነበር። ይህ ገቢ እ.ኤ.አ በ2034 ወደ 186 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያድግ ተገምቷል።

በታይላንድ የሚገኘውና በጤና ቱሪዝም መስክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው ቡምሩንግራድ ኢንተርናሽናል ሆስፒታል መረጃ እንደሚያመላክተው፣ ታይላንድ እ.ኤ.አ በ2019 ብቻ ከ3 ሚሊዮን በላይ የውጭ ታካሚዎችን በመሳብ ወደ 600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝታለች። በታይላንድ የጥርስ ህክምና፣ የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና እና የአጥንት ህክምና ከሌሎች ሀገራት ባነሰ ወጪ ማግኘት ይቻላል። ብዙ የታይላንድ ሆስፒታሎች ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኙ ሲሆን፣ የሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎችም በዓለም ታዋቂ ከሆኑ ተቋማት የሰለጠኑ በመሆናቸው ለታካሚዎች ጥራት ያለው አገልግሎት ይሰጣሉ። ለሀገሪቱ የጤና ቱሪዝም ስኬት ሌላኛውና ወሳኝ ምክንያት ተደርጎ የሚወሰደው የሀገሪቱ ውብ የባህር ዳርቻዎች፣ ማራኪ ባህል እና የተለያዩ መስህቦች ያላት በመሆኑ፣ ታካሚዎች ከህክምናቸው ጎን ለጎን ዘና ያለ ጊዜ እንዲያሳልፉ እድል መፍጠራቸው ነው።

እ.ኤ.አ በ2023 ለንባብ በበቃው የግሎባል ሄልዝ አክሪዲቴሽን (Global Healthcare Accreditation) መረጃ መሰረት ህንድ በጤና ቱሪዝም ዘርፍ እንደ ዋና ተዋናይ የምትጠቀስ ሌላኛዋ ሀገር ነች። ሀገሪቱ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ውስብስብ የልብ ቀዶ ጥገና፣ የካንሰር ህክምና እና የአካል ክፍሎች ንቅለ ተከላ የመሳሰሉ አገልግሎቶችን ትሰጣለች። ለጤና ቱሪስቶች የተመቻቸ የቪዛ አሰራር መኖሩ ብዙ ሰዎች ህንድን እንዲመርጡ የሚያግዝ ሲሆን፣ በዚህም የጤና ቱሪዝም ዘርፍ የሀገሪቷ ዓመታዊ ገቢ በ2022 ወደ 7 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር ደርሶ እደነበር መረጃው ያሳያል።

የጤና ቱሪዝም ማህበርን ዋቢ አደርገን ስንቀጥል በሕክምና ቱሪዝም ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት ከሚሰጡ ሀገራት መካከል አንዷ ማሌዢያን ናት፡፡  እ.ኤ.አ ከ2011 ጀምሮ የጤና ቱሪዝም በማሌዥያ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ የመጣ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2019 ብቻ ወ? 1 ??? 22 ???? ???? ??? ????? ????? ??????? ???? ???? 375 ???? ????? ??? ?? ??????? ???? ????? ??????? ???? ????? ?????? ??????? ???????? ?????ደ 1 ነጥብ 22 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ለህክምና ወደዚያው ተጉዘዋል፡፡ በዚህም ሀገሪቱ 375 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ አግኝታለች። ሀገሪቱ የተለያዩ ህክምናዎችን ማለትም የወሊድ፣ ኦንኮሎጂ፣ ካርዲዮሎጂ፣ ኦርቶፔዲክስን የመሳሰሉትን ህመሞች ለማከም የሚያስችል ቴክኖሎጂ ታጥቃለች። በተከታታይ “የዓመቱ ምርጥ የጤና ቱሪዝም መዳረሻ” ተብላ በመመረጧ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አግኝታለች።

በጤና ቱሪዝም አገልግሎት ዕድገት ሳትጠቀስ የማትታለፈውና በተለይ በፀጉር ንቅለ ተከላ እና በኮስሞቲክስ (የውበት ቀዶ ጥገና) ህክምናዎች የምትታወቀው ቱርክ በዘርፉ ፈጣን ዕድገት እያሳየች ያለች ሀገር ስትሆን፣ በ2022 ወደ 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘት ችላለች፡፡ ይህም በ2024 ወደ 3 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።

አህጉረ አፍሪካ በዘርፉ ያለችበትን ደረጃ ለማመላከት ይረዳ ዘንድ የአንዳንድ ሀገራትን ተሞክሮ እንጥቀስ፡፡ የጤና ቱሪዝም በአፍሪካ እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ቢሆንም፣ ከሌሎች የዓለም ክልሎች ጋር ሲወዳደር ገና በጅምር ላይ ያለ ነው ማለት ይቻላል። በዘር ተወዳዳሪ ለመሆን በመሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና በባለሙያዎች ስልጠና ላይ ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ እንደሚያስፈልግ የዘርፉ ባለሙያዎች ይስማማሉ።

ይሁንና የሰሜን አፍሪካ ሀገሮች በተለይም ቱኒዚያ እና ግብፅ በጤና ቱሪዝም ዘርፍ በቀዳሚነት ተጠቃሽ ሀገራት ናቸው። ቱኒዚያ በውበት ቀዶ ጥገና፣ በጥርስ ህክምና እና በሌሎችም ህክምናዎች ከአውሮፓ እና ከሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚመጡ ብዙ ታካሚዎችን ታስተናግዳለች። ግብፅም የህክምና አገልግሎቷን ከቱሪዝም መስህቦቿ ጋር በማጣመር ከፍተኛ ትኩረት አግኝታለች።

ከሰሜን አፍሪካ ውጭ ባሉ ሀገሮች ውስጥ ደግሞ ደቡብ አፍሪካ በህክምና ተቋሞቿ ጥራትና ተመጣጣኝ ዋጋ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ታካሚዎችን በመሳብ ቀዳሚ ሀገር ናት። ናይጄሪያ በምዕራብ አፍሪካ፣ ኬንያ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለመሆን እየጣሩ ነው።

ምንም እንኳን አንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ከጤና ቱሪዝም ገቢ የሚያገኙ ቢሆንም፣ አፍሪካ በአጠቃላይ ለህክምና ወደ ውጭ ሀገራት ለሚጓዙ ዜጎቿ በየዓመቱ ከፍተኛ ገንዘብ ታወጣለች። የአፍሪካ ኤክስፖርት-ኢምፖርት ባንክ እንደገለጸው፣ አፍሪካ በየዓመቱ ወደ 7 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር በጤና ቱሪዝም ምክንያት ታወጣለች። ናይጄሪያን ብቻዋን  በየዓመቱ እስከ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ታወጣለች።

ወደ ኢትዮጵያም መለስ ስንል አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንስቃሴዎች እንደተጀመሩና በመንግስት ደረጃ ከሚሰሩ ስራዎች ባሻገር የግሉን ክፍለ ኢኮኖሚ በማሳተፍ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በቅርቡ መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡

ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የ2017 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት እና የ2018 በጀት ዓመት ዋና ዋና አቅጣጫዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፣ የጤና ቱሪዝምን ከማሳካት አንፃር በርካታ ጥረቶች እየተደረጉ ነው። ለአብነትም በኮልፌ ቀራንዮ እና በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተሞች የሁለት አዳዲስ ግዙፍ አጠቃላይ ሪፈራል ሆስፒታሎች ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል። እንዲሁም የጥሩነሽ ቤጅንግ፣ የራስ ደስታ፣ የዘውዲቱ ሆስፒታል እና ሚኒሊክ ሆስፒታል እየተሰራ ያለው ግዙፍ ማስፋፊያ እየተጠናቀቀ ነው፡፡ በሌላ በኩል ስምንት አዲስ ጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው የተጠናቀቀና በቅርቡ ስራ የሚጀምሩ ሲሆን፣ በተያያዘ በአራት ነባር ሆስፒታሎች እና ሌሎች ተጨማሪ ጤና ጣቢያዎች የተቋማቱን አቅም በሚያሳድግ መልኩ ሰፊ እድሳቶች ተሰርተዋል፡፡

የጤና ቱሪዝም ማህበር መስራች የሆኑት ጆናታን ኤደልሃይት እንደሚሉት ሀገራት በጤና ቱሪዝም ዘርፍ ከገንዘብ ባሻገር የሚያገኟቸው ጥቅሞች በርካታ ናቸው። የውጭ ታካሚዎችን ለመሳብ ሲባል ሀገራት በዘመናዊ የህክምና ቴክኖሎጂዎችና መሳሪያዎች ላይ መዋዕለ ንዋይ ያፈስሳሉ። ይህም የህክምና አገልግሎት ጥራት እንዲጨምርና የሀገር ውስጥ ታካሚዎችም ዘመናዊ ህክምና እንዲያገኙ ይረዳል። በተጨማሪም፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመወዳደር ሲባል የአካባቢው የህክምና ባለሙያዎች አዳዲስ እውቀቶችንና ክህሎቶችን ይማራሉ።

ጆናታን ኤደልሃይት ሲቀጥሉም ከህክምና አገልግሎት በተጨማሪ፣ በህክምና ቱሪዝም ዙሪያ የተለያዩ የሥራ ዕድሎች ይፈጠራሉ። እነዚህም በሆቴሎች፣ በትራንስፖርት አገልግሎት፣ በቱሪዝም አስጎብኚነት፣ በትርጉም አገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ ያሉ ሥራዎችን ያካትታሉ። አንድ ሀገር የህክምና ቱሪዝም ስኬታማ መዳረሻ መሆን ሲችል፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ገጽታ ከፍ ይላል፡፡ የህክምናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን የሀገሩ አጠቃላይ የቱሪዝም እና የኢኮኖሚ ጥንካሬም ጎልቶ ይታያል ይላሉ።

የጤና ቱሪዝም ዘርፍ በፍጥነት እያደገ ያለ ኢንዱስትሪ ሲሆን፣ በየጊዜው አዳዲስ ፈጠራዎችን እያሳየ የሚገኝ ዘርፍ ነው። ከእነዚህም መካከል የቴሌ መድኃኒት (Tele medicine)፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና ሮቦቲክስ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ለማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ አሁን ላይ የርቀት ህክምና አገልግሎትም እየተስፋፋ መምጣቱ ታካሚዎች ወደ ሌላ ሀገር ከመጓዛቸው በፊት ከውጭ ሀኪሞች ጋር በቪዲዮ መገናኘት፣ የምክር አገልግሎት ማግኘት እና ለቀዶ ጥገናም ሆነ ለሌላ ህክምና መዘጋጀት ይችላሉ።

በሌላም በኩል ሰው ሰራሽ አስተውሎት በጤና ቱሪዝም ውስጥ የተለያዩ ሚናዎችን እየተጫወተ ይገኛል። ሰው ሰራሽ አስተውሎት ታካሚዎች የህክምና መረጃዎችን እንዲያገኙ፣ የተሻለ ሆስፒታል ወይም ሀኪም እንዲመርጡ፣ እንዲሁም ለጉዟቸው የተስማማ ዕቅድ እንዲያዘጋጁ ይረዳቸዋል። እንደዚሁም እንደ ሮቦት ቀዶ ህክምና ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች በጤና ቱሪዝም ውስጥ ተጽኗቸው እያደገ መጥቷል ይላል ከላይ የጠቀስነው የጤና ቱሪዝም ማህበር መረጃ፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review