ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን -ጎሮ-ቦሌ አየር መንገድ ቪአይፒ ተርሚናል ያለዉ የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገለጹ

You are currently viewing ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን -ጎሮ-ቦሌ አየር መንገድ ቪአይፒ ተርሚናል ያለዉ የኮሪደር ልማት ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገለጹ

AMN ነሃሴ 24/2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬም ሌላኛው ብስራታችን የሆነውን ከአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን-ጎሮ-ቦሌ አየር መንገድ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር አጠናቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።

የሁል ጊዜ ህልማችን እውን የሚሆነው በየእለቱ፣ በየሰዓቱ፣ በየደቂቃው ያለረፍት በመስራታችን ነው። ይህ ኮሪደር በሁለተኛ ዙር ከጀመርናቸዉ ስምንቱ ኮሪደሮች አንዱ እና ከተጠናቁት ደግሞ 4ኛዉ ሲሆን አዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽን ማእከልን ከቦሌ ኤርፖርት ቪአይፒ ተርሚናል የሚያገናኝ፣ ከአንበሳ ጋራዥ – ጃክሮስ ጐሮ እና በኮሪደር አንድ ከተሰራው ቦሌ ኤርፖርት መገናኛ ሲኤምሲ ጋር የሚገጥም ነው ብለዋል።

የኮሪደሩ አጠቃላይ ስፋት ከ290 ሄክታር በላይ ሲሆን 12.74 ኪሎ ሜትር ርዝመት እንዲሁም 29.446 ኪሜ የሚረዝም የእግረኛ መንገድ ያለው ነው። በተጨማሪም 15.27 ኪሎ ሜትር የብስክሌት መንገድ፤ ከ550 በላይ ታክሲና ባሶችን የመያዝ አቅም ያላቸው 5 የባስና የታክሲ ተርሚናሎች፤ ከ800 በላይ መኪኖችን የመያዝ አቅም ያላቸው 4 ፓርኪንግን ጨምሮ ታክሲና ባስ መጫኛና ማውረጃ 17 ቤይ ተሰርቶለታል።

ዛሬ ለህዝብ ክፍት ያደረግነው ይህ ኮሪደር 5 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት እና 2 ድልድዮች እንዲሁም 12 ኪ.ሜ የጎርፍ መውረጃ ቱቦ ዝርጋታን ጨምሮ 3.6 ኪ.ሜ የመጠጥ ውሃ ዝርጋታ እና 669 የመንገድ ዳር መብራቶች ተሰርቶለታል ብለዋል። ትላልቅና መካከለኛ ካፌዎች ፤ 41 መጸዳጃ ቤቶች ፤ 9 የህጻናት መጫወቻ ቦታዎች እና 7 የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን ጭምሮ 4 ፕላዛዎች እና 130 ሄክታር የሚሸፍን የወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማትንም አካቷል።

ይህ የኮሪደር ልማት እንደ ሌሎቹ ኮሪደሮች ሁሉ ለነዋሪዎቻችን ሰፊ የስራ እድል የፈጠረ፣ ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ የፈጠረ፣ አካታች እና ሁሉንም ሰዉ ከልማቱ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ ከ320 በላይ ህንፃዎች እድሳት በማድረግ እና ከ350 በላይ የንግድ ሱቆች በመክፈት የንግድ እንቅስቃሴው በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ያደረገ፣ የመንገድ መጨናነቅን ችግር በመፍታት የትራንስፓርት ፍሰቱን የሚያቀላጥፍ እና የተለያዩ የአገለግሎት መስጫዎችን ያሻሻለ ውጤታማ ስራ ነው።

ይህ ኮሪደር በታለመለት ጊዜ እና በጀት እንዲጠናቀቅ ደከመን ሰለቸን ሳትሉ ለተሳተፋችሁ ባለሞያዎች፤ አመራሮች እና የአካባቢው ማህበረሰብ በሙሉ በከተማ አስተዳደሩ እና በራሴ ስም ላመሰግናችሁ እወዳለሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review