የሠላም አማራጭ የተከተሉ የቀድሞ ታጣቂዎች ሠላምን በማፅናት ሕዝብና መንግስትን ለመካስ ዝግጁ መሆን አለባቸው ሲሉ የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጄኔራል ደርቤ መኩሪያው ተናገሩ።
በጠዳ ተሀድሶ ስልጠና ማዕከል የገቡ የቀድሞ ታጣቂዎች የተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ዛሬ ተካሂዷል። በስልጠና መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የተገኙት የብሔራዊ ተሀድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነሩ እንደተናገሩት፤ የቀድሞ ታጣቂዎችን በአጭር ጊዜ መልሶ በማቋቋም ዘላቂና ሠላማዊ ሕይወት እንዲመሩ ኮሚሽኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው።
ሕዝቡ አጥብቆ ሠላም ይሻል መንግስትም የጀመራቸውን ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ማስቀጠል ይፈልጋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፥የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላም ሃይል በመሆን የበደሉትን ሕዝብና መንግስት በልማት መካስ አለባችሁ ብለዋል። ኮሚሽኑ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች እስካሁን የሠላም አማራጭን የተቀበሉ ከ74ሺ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች ወደ ሠላማዊ ሕይወት ለመመለስ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አንስተዋል።
በአማራ ክልል ከ11 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በተሀድሶ ፕሮግራም እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። መንግስት ትናንትም ዛሬም ሆነ ነገ ቅድሚያ የሚሠጠው ለሠላም ነው ያሉት በብልጽግና ፓርቲ የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ይርጋ ሲሳይ ናቸው።

መንግስት ችግሮች በሠላማዊ ውይይትና ንግግር ተጀምረው እንዲቋጩ ፍላጎት እንዳለው አንስተው፤ በክልሉ አሁን ላይ ሠላም መስፈኑን ገልጸዋል። የቀድሞ ታጣቂዎች ሠላምን አማራጭ ማድረጋቸው ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው፤ ነገ ለመንግስትና ለሕዝብ ታማኝ በመሆን ሠላማዊ ሕይወት እንዲመሩ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ(ዶ/ር)፤ የቀድሞ ታጣቂዎች ግጭት አይጠቅምም በማለት የሠላም አማራጭን መከተላቸው የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰሜን ምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥ ብርጋዴል ጄኔራል ዋኘው አለሜ እንዳሉት፥ሕዝቡ ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመቆም ለሠላም ባለው ቁርጠኝነት ባደረገው ጥረት አሁን ላይ ሠላምን ለማፅናት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
የቀድሞ ታጣቂዎች የሠላምን አማራጭ ተቀብለው የሠላም ሃይል ለመሆን መወሰናቸው ተገቢ መሆኑን ጠቁመው፤ በጥፋት መንገድ ለመቀጠል የሚሞክሩትን አጥበቀው ሊታገሏቸው እንደሚገባ ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ በተሀድሶ ስልጠና ማስጀመሪያ ሥነ-ሥርዓት ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የጎንደር ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች የሀይማኖት አባቶችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።