በሩሲያ የሚደረገውን ሁለተኛው ዙር ኪን-ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ጉዞን በተመለከተ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እና የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ከሻኩራ ፕሮዳክሽን ጋር በመሆን መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋሁን ጎበዛይ እንዳሉት ኪን ኢትዮጵያ ጉዞ ኢትዮጵያን በልኳ ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።
በህዝብ ለህዝብ ግንኙነትና ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አስፈላጊ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ ኪነጥበብ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በቻይና ለሶስት ቀናት በነበረው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ በቻይናና ኢትዮጵያ መካከል ያለውን የመንግስት ለመንግስት ግንኙነት በህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር ትልቅ ሚና ተወጥቷል ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጭ ለማስተዋወቅ እድል የፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፥ ቀጣይነት ያለው የህዝብ ለህዝብ ትስስርና ንግድና ኢንቨስትመንት ልውውጥ ለማጠናከር የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ጉዞው የሁለትዮሽ ውይይቶችና ስምምነቶች የተደረገበት መሆኑን በመግለፅ፥ ኹነቱ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ሽፋን ማግኘቱንም ተናግረዋል።
የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ የኢትዮጵያን መልክ ለአዓለም በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ሚና እየተወጣ ነው ብለዋል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው ሁለተኛው የኪን ኢትዮጵያ ጉዞ ከጳጉሜ 4 ቀን 2017 እስከ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም በሩሲያ እንደሚደረግ መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ጉዞው የኢትዮጵያና ሩሲያን የባህል ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።
በሴንት ፒተርስበርግና ሞስኮ በሚካሄደው የጥበብ ትዕይንት የተለያዩ ኹነቶች እንደሚካሄዱም ተናግረዋል።
በጉዞው የሚሳተፈው የኪን ኢትዮጵያ ቡድን በሩሲያ በሚካሄደውና ከ60 በላይ ሀገራት የባህልና ጥበብ ተወካዮች በሚሳተፉበት የዩናይትድ ካልቸራል ፎረም የተለያዩ ትዕይንቶችን ያቀርባል ብለዋል።