አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በምትወስዳቸው ዘርፈ ብዙ ዕርምጃዎች የአህጉሪቱ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ

You are currently viewing አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በምትወስዳቸው ዘርፈ ብዙ ዕርምጃዎች የአህጉሪቱ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው ተገለጸ
  • Post category:አፍሪካ

AMN- ነሐሴ 30/2017 ዓ.ም

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የሚደርስባትን ተፅዕኖ ለመቋቋም በምትወስዳቸው ዘርፈ ብዙ ዕርምጃዎች የአህጉሪቷ ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ መሆን እንዳለባቸው የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለፁ።

የአፍሪካ ሁለተኛው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አካል የሆነው የአፍሪካ የወጣቶች የአየር ንብረት ጉባኤ በዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ነው።

በመድረኩ ለአፍሪካ ወጣቶች ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ቀዳሚ ተጎጅዎች ሴቶች፣ ህፃናትና ታዳጊዎች በመሆናቸው ለችግሩ እልባት ለመስጠት ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ በአንድ ጀንበር ችግኝ ተከላ ወጣቶች በንቅናቄ እንደሚሳተፉ ያብራሩት ሚንስትሯ፣ ይህም ችግኝ ከመትከል ባለፈ የነገዋን ኢትዮጵያ ለወጣቶች የማስረከብ ሂደት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በአንድ ጀንበር ከ700 ሚሊየን በላይ ችግኞችን በመትከል የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም በትኩረት እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል።

የአፍሪካ ወጣቶች በሁለተኛው የአየር ንብረት ስብሰባና በኮፕ-30 በአንድ ላይ ድምፃቸውን ለማሰማት የጋራ ራዕይ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።

የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ በሁሉም የልማት ዘርፎች ለወጣቶች ተሳትፎ ቅድሚያ እንደምትሰጥ ገልፀው፣ አካታች አህጉራዊ የወጣቶች ትብብር ላይ በትኩረት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን በመወከል በጉባኤው የሚሳተፉ ወጣቶችም ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ወጣቶችና አደረጃጀቶች ጋር የልምድ ልውውጥ እያካሄዱ ሲሆን፣ ጉባኤው ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይም ተመላክቷልል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review