በቀደምቶቻችን ደም እና ዐጥንት ፀንታ የኖረች አገራችንን በላቀ ደረጃ ታፍራ እና ተከብራ እንድትቀጥል የዐዲስ ምዕራፍ ጎዞ ላይ እንገኛለን፡፡
በየታሪክ አንጓዉ ያጋጠሙ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ ዐዲስ ታሪክ የሚሠሩ ጀግኖች
ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ፡፡
በየታሪክ አንጓዉ ለሚከናወኑ ገድሎች ደግሞ ባለቤቶቹ ሲኖሩ ኢትዮጵያዊ ሲሞቱ ኢትዮጵያ መኾን የሚያሳሳቸዉ ውድ ልጆቿ ናቸው፡፡
ለዚህም ነው ጳጒሜን አንድን “ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር” በሚል መሪ መልእክት በሀገር አቀፍ ደረጃ እነዚህን ጀግኖቻችን ለማመስገን የምናከብረው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘመናት በችግሮች እና ፈተናዎች ያልተንበረከከች የታሪክ እና ትርክት ገመዶቿ እጅግ የተሳሰሩ ሀገር ናት፡፡
በዓድዋ ድል ዋዜማ የከብቶች በሽታ እና ድርቅ ከእርስ በርስ ሽኩቻ ጋር ኢትዮጵያን እየፈተኑ ነበር፡፡
ፅኑ የሀገርነት መሠረት እንደነበረን ያልተገነዘበ ጠላት ወረረን፤ ጀግኖች ቀደምቶቻችን የእርስ በርስ ሽኩቻዉን ትተው፣ ድርቅና የእንስሳት እልቂት ያስከተሉትን ጫና ተቋቁመዉ ወደ ዓድዋ ዘመቱ፤ የዓለምን ታሪክ ከዓድዋ በፊትና በኋላ ብሎ የከፈለ ድል አስመዝግበዉ ብርቱ ሀገር አስረከቡን፡፡
በዚህኛዉ ክፍለ ዘመንም ዐዲስ የታሪክ አንጓ የፈጠረች ብርቱ ሀገር ናት፤ ኢትዮጵያ፡፡ ከሕዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ የሚል ሌላ የታሪክ አንጓ በፈተናዎች አልፋ አሳክታለችና፡፡
ይህንን የታሪክ መታጠፊያ አንጓ ለመፍጠር ጠንካራ እና ለምንም የማይበገር ሀገር የመገንባት ቁርጠኝነት ይጠይቅ ነበር፡፡
ድርቅ፣ ጎርፍ፣ ጦርነት፣ የኮቪድ-19
ወረርሽኝ፣ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ፣ የመሬት መንሸራተት፣ የዓለማቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ጫና መብዛት፣ የታሪካዊ ጠላቶቻችን በየቦታዉና በየጊዜዉ የተንኮል ጉድጓድ መቆፈር ወ.ዘ.ተ. የኅዳሴ ግድባችን ፈተናዎች ነበሩ፡፡
ይሁን እንጅ ፈተናን ተጋፍጦ፣ እንደ ወርቅ ተፈትኖ የሀገር ሉዓላዊነትን ማፅናት እና ታሪክ መሥራት ለኢትዮጵያውያን መገለጫቸው ነውና ሊነጋ ሲል የነበረዉን ጨለማ በኅዳሴ ብርሃን ገልጸውታል፤ ፈተናዎችን ኹሉ በድል ተሻግረዉ የኢትዮጵያን ታሪክ ከታላቁ ኅዳሴ ግድብ በፊት እና በኋላ በሚል አንጓ ከፍለውታል፡፡
ለዚህም በየግንባሩ በነበረዉ ተጋድሎ ኢትዮጵያ የኾኑ ኢትዮጵያውያን ፅኑ መሠረት ያላት ብርቱ ሀገርን ገንብተውልን ዐልፈዋል፤ ዘልዓለማዊ ክብርም ከዛሬ እስከ ነገ እንሰጣቸዋለን፡፡
ከታሪካችን የተማርነው ኢትዮጵያዊ ስለኢትዮጵያ የሚተባበር፣ ስለኢትዮጵያ ሕይወቱን በደስታ የሚገብር፣ ስለኢትዮጵያ ምድራዊ ፈተናዎችን ኹሉ በቁርጠኝነት የሚቋቋምና ለድል የሚበቃ ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር ለማስቀጠል የሚታትር ነው፡፡
ይህንን የልጆቿን ጥረት እና ፍቅር ደግሞ ኢትዮጵያ መቼም አትረሳም፡፡
እንኳን ለጳጉሜን 1፣ የጽናት ቀን በሰላም አደረሳችሁ!
የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት
ጳጉሜን 1
የፅናት ቀን
“ፅኑ መሠረት ብርቱ ሀገር”