“ሕዝቡ ከተማዋን ለመቀየር በመወሰኑና የከተማዋ ማማር ለእኔው ነው ብሎ በመሥራቱ ጥሩ ውጤት
ማየት ችለናል”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
አሁን ላይ እንደ አዲስ ውልድ ጨቅላ ሲመለከቷት የምታሳሳው አዲስ አበባ ለዓመታት እንደስሟ መሆን የተሳናት የሚል ትችት ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡ ከጄኔቫ እና ኒው ዮርክ ቀጥላ ሦስተኛዋ የዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከል የሆነችው መዲናዋ ገጽታዋ ዝናዋን የሚመጥን እንዳልሆነና ንጽህናዋም ስምና ክብሯን የሚመጥን እንዳልነበር ብዙዎች ይስማማሉ፡፡
ከ130 በላይ ኤምባሲዎች፣ የበርካታ ሀገራት ቆንጽላ ጽሕፈት ቤቶች የሚገኙባት፣ እንደ አፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽንን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትን በጉያዋ የያዘች ከተማ ምን ቢጎድላት ለትችት ተዳረገች? ባለፉት ጥቂት ዓመታትስ ለሚነሱባት ትችቶች እልባት ለመስጠት ምን ሰራች? የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢነት ይኖረዋል፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ከተማዋ በአዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት መልኳን መቀየር ጀምራለች፤ ‘መቆሸሽ ዕጣ ፈንታዬ አይደለም’ ብላ ወደ ስራ የገባች ትመስላለች፡፡ ለብዙ ዓመታት ሳይታደሱ የቆዩ የከተማዋ አካባቢዎች አሁን ዘመናዊውና ማራኪ መልክ በመያዛቸው የከተማዋን ገጽታ ለውጠውታል። ለዚህም በርካታ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን፣ ፓርኮችን፣ መንገዶችን፣ የመስህብ ስፍራዎችን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
በተለይም አይነተ ብዙ ልማቶችን የሚያቅፈው የኮሪደር ልማት ስራ የመዲናዋን ሽፍንፍን ገልጦ ልዩ ውበት አላብሷታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማት ዘላቂነት ባለው አግባብ ለነዋሪዎቿ ኑሮ የተመቸችና የላቀች፣ ውብ መኖሪያ ከተማ የማድረግ ዘመን ተሻጋሪ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው ነበር። አዲስ አበባን መልሶ በመገንባት ሂደት ስሟን የሚመጥን፣ ‘እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን፣ ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ እንሰራለን’ በማለት የተገባውን ቃል የመፈጸም ሂደት መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከትናንት በስቲያ ከመስቀል አደባባይ እስከ መገናኛ ያለውን የ8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማትን ባስመረቁበት ወቅት እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተማ በተሠሩ የኮሪደር ልማቶች ልዩ ከተማን የመገንባት ጅማሮ የታየባቸው ናቸው፡፡ ሰሞኑን የተመረቀው 8 ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት 16 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ፣ 15 የመኪና ማቆሚያ እና የታክሲ መጫኛዎች እንዲሁም 15 ለሕዝብ የሚሆኑ መናፈሻዎች፣ የልጆች የመጫወቻ ቦታዎች፣ የስፖርት ሜዳዎች ተሰርተዋል፡፡ ስፍራው ብዙ ሕንፃዎች ያሉበት ቢሆንም በተገኘው ቦታ ላይ ግን ጥሩ እና በቂ ነገር ስለመሰራቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስምንት ኮሪደሮችን ለመስራት መታቀዱን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሰሞኑን የተመረቀው አምስተኛው ኮሪደር ልማት እንደሆነ ጠቁመዋል። “ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ባሰብነው ልክ እና ከአንደኛው ዙር በተሻለ መልኩ አጠናቅቀናል፤ ለሕዝባችን በገባነው ቃል መሠረት ከአዲሱ ዓመት በፊት አብዛኛውን ሥራዎች ሠርተናል” ሲሉም አክለዋል። የአዲስ አበባ ሕዝብ የከተማዋ ባለቤት ሆኖ ከተማዋን ለመቀየር በመወሰኑ እና የከተማዋ ማማር ለእኔው ነው ብሎ በመሥራቱ ጥሩ ውጤት ማየት ችለናልም ሲሉ ተናግረዋል።
ከተማዋ ለቱሪስት አገልግሎት ምቹ፣ ለፋይናንሻል ሴክተር እና ለቴክኖሎጂ ምንጭ መሆን አለባት ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ። ኢንዱስትሪዎች እና የማዕድን ሴክተሩ ከከተማ ወጣ በማድረግ በከተማ መሐል ላይ ሆቴሎች፣ ሞሎች፣ ሆስፒታሎች ኖረው ቱሪስቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ እና ገቢ እንዲገኝ ለአገልግሎት የሚያስፈልጉ ጉዳዮችን ሟሟላት እንደሚገባም ገልጸዋል።
በከተማዋ የመጡት ለውጦች በቀላሉ የተሳኩ እንዳልሆኑ ጠቁመው፤ ሕዝቡ ለማደግ፣ ለመለወጥ እና የተሻለ ከባቢን ለመፍጠር የሚከፈለውን ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ መሆን እንዳለበት አስገንዝበዋል። አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ የልማት ሥራዎች የተሠሩ ቢሆንም አሁንም ግን በርካታ አሮጌ መኪናዎች ስላሉ በበቂ ደረጃ አየሩ የፀዳ አይደለም፤ በዚህ ላይ ተጨማሪ ሥራዎች በሚቀጥሉት ዓመታት ይሥራል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
5ኛውና ከመስቀል አደባባይ – መገናኛ – ሳውዝጌት ያለው የ8 ኪሎ ሜትር ኮሪደር ልማት በተመረቀበት ወቅት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት የተሰሩት የኮሪደር ልማት ስራዎች ሁሉንም የማህበረሰብ ክፍሎች ታሳቢ ያደረጉ ናቸው፡፡
በዋናነት ትኩረት የሚሰጠው ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ ላይ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ አዲስ አበባ በኮሪደር ልማቱ ለህዝብ ስፍራ ያላት፣ ለጋራ መገልገያ ቦታዎች የምትሰጥ እና ኢንቨስት የምታደርግ ከተማ መሆኗን ያሳየንበት ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡ ሁል ጊዜ ህዝባችንን ለማገልገል ያለእረፍት እንሰራለን ያሉት ከንቲባዋ፤ እነዚህ ልማቶች የተሰሩት ከከተማዋ ማህበረሰብ ጋር በመሆኑ ለዚህም ምስጋናችን ከፍ ያለ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የከተማዋ መንገዶች እና ኮሪደሮች ለውጥም በገጽታዋ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል። አዳዲስ አውራ ጎዳናዎች፣ የፍጥነት መንገዶች እና የጎዳና ላይ መብራቶች የከተማዋን ገጽታ ዘመናዊ አድርገውታል። የጎብኝዎች ፍሰት የጨመረባቸው እንደ ብሔራዊ ሙዚየም ያሉ በርካታ ታሪካዊ እና ባህላዊ ስፍራዎች ታድሰው አገልግሎት እየሰጡ ነው። እነዚህም ቦታዎች የከተማዋን ቅርስ እየጠበቁ ለቱሪዝም እንዲያገለግሉ ተደርገዋል።
ከአረንጓዴ ልማት ውጪ ከተማን ማልማት የማይታሰብ ነው የሚሉት ሲዊዲናዊው (Urban Forestry & Urban Greening) መጽሐፍ ደራሲ ክርስቲያን ሃላንድ በተለይ በከተሞች ንጹህ አየር ያላቸው አረንጓዴ ስፍራዎች ካልተያዙ፣ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ ካልተመቹና ልጆችን ለማዝናናት የሚመቹ ካልሆኑ ከተሞች ህይወት አላቸው ማለት አይቻልም ይላሉ፡፡
ይህንን የተረዳችው አዲስ አበባ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ አዳዲስ እና የታደሱ ፓርኮችና አረንጓዴ ስፍራዎችን ሰርታለች። የእንጦጦ ፓርክ፣ ብሔራዊ ሙዚየም፣ አንድነት ፓርክ ከከተማዋ ትልልቅ የመዝናኛ ስፍራዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው። በአንድነት ፓርክ ውስጥ የሚገኙት ታሪካዊ ህንጻዎች፣ ንጹህ አረንጓዴ ስፍራዎችና መዝናኛዎች ከተማዋን ለጎብኝዎች የበለጠ ማራኪ አድርገዋታል። ሸገር ፓርክ እና ሌሎች አነስተኛ ፓርኮች ለከተማ ነዋሪዎች ንጹህ አየር የሚወስዱባቸውና የሚዝናኑባቸው ስፍራዎችን በመስጠት የከተማዋን አረንጓዴ ሽፋን አሳድገዋል።
ባለቤት አልባ ውሾች የወደቀውን ለመጋራት ሲጣሉና ሲናከሱ ይታዩባቸው የነበሩ የአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎቿና ወንዞች ዛሬ ላይ ለማየት ያሳሳሉ። ለዚህም ዝነኛው የግንፍሌ ወንዝ በእማኝነት ጠቅሰን እንለፍ፡፡ ቀለማቸው ተዘበራርቆና ወይበው የነበሩ የከተማዋ ሕንፃዎች ሳይቀር አስታዋሽ አግኝተው የመዲናዋ አሁናዊ የውበት ገጽታ ማሳያ ተደርገው የሚወሰዱ ሆነዋል፡፡ በዚህ ላይ የመዝናኛና የመናፈሻ ቦታዎች፣ የልጆች መጫዎቻና የሕዝብ ፕላዛዎች፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የውሃ ፋውንቴኖች እንዲሁም ጎዳናዎቹን ውበት የሚያላብሱ የመንገድና የህንጻ ላይ መብራቶች ስንጨምርበት ስም ከግብር ገጠመ ለማለት ያስችላል፡፡
እዚህ ጋር የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑትን አቶ ምንዳዬ እንዳለን በምስክርነት እንጥቀስ። አቶ ምንዳዬ እንደሚሉት በተለያየ ምክንያት በመዲናዋ በተለያዩ አካባቢዎች ኖረዋል፡፡ ከተማዋን የከዚህ ቀደም ሁኔታ ሲገልጹ በከተማዋ ለብዙ ዓመታት ስለኖርኩኝ ገመናዋን ጠንቅቄ አውቃለሁ፡፡ ጭርንቁስ ሰፈሮቿንም እንደዚሁ፡፡ በተለይም በምሽት መንቀሳቀስ የሚታሰብ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ትንሽ መሸት ሲልም ጭምር ከቤተሰብ ጋር ለመንቀሳቀስ ምቹና ንፁህ አካባቢዎች ተፈጥረዋል ይላሉ፡፡ አያይዘውም ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የምንኖርበት አከባቢ ምቹ ስለሆነ ከጓደኞቼ ጋር እንቅስቃሴ ለማድረግና አረፍ ብለን ለመወያየት ከፒያሳ፣ አራት ኪሎ መገናኛ ያለውን መንገድ ምቹ ሆኖ አግኝተነዋል ይላሉ አቶ ምንዳዬ፡፡
አቶ ምንዳዬን ጨምሮ ሌሎች ሀሳባቸውን ያካፈሉን የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት በርካታ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሚደረግባትና ያለ ዕድሜ ገደብ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የምትቀበለው አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ዘመን ያነሳት ይመስላል፡፡ መዲናዋ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገረችና እያንሰራራች ስለመሆኑ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ የልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ ከማሻሻላቸው ባሻገር ለነዋሪዎች የተሻለ የኑሮ ሁኔታ እና የስራ ዕድሎችን እየፈጠሩ ስለመሆኑም አስተያየት ሰጪዎቹ ያነሳሉ።
እስካሁን በተሰሩትና በግንባታ ላይ የሚገኙት ሥራዎች ሲጠናቀቁም አዲስ አበባ እንደ ስሟ ውብ እና እንደ ክብሯ ይበልጥ ከፍ ማለቷ የሚቀር አይመስልም። በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ፕላን ባለሙያ መስፍን አለሙ በበኩላቸው፣ ከተማዋ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ያከናወነቻቸውና ገጽታዋን የቀየሩት ስራዎች በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት ያስረዳሉ፡፡ ስራዎቹ የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየራቸውም ባሻገር የመንገድ፣ የውሃ፣ የመብራት፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮችና ሌሎችም ደረጃቸውን በጠበቀ ሁኔታ የማሻሻል ስራ ተከናውኖበታል። የመንገድ መሰረተ ልማቶቹም ለተሽከርካሪዎች፣ ለእግረኞች፣ እንደዚሁም ለሁለት እግር ተሽከርካሪ ለሚጠቀሙ የተፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀላል አይደለም፡፡ የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ የቱሪዝም ፍሰትን የጨመሩ እና የህዝቡን አኗኗር ያዘመኑ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የከተማ ፕላን ባለሙያው ጨምረው እንዳብራሩት፣ በከተማዋ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እርስ በእርሳቸው የተሰናሰሉ በመሆናቸው ለመዲናዋ ልዩ ውበት ሰጥተዋታል፡፡ የባለሙያውን አስተያየት ማረጋገጥ ካስፈለገ ፒያሳ፣ ሜክሲኮ፣ መገናኛ፣ ቦሌ እና ሌሎችም የኮሪደር ልማት ስራው የተጠናቀቁባቸው አካባቢዎች መገኘት ብቻ ይበቃል። መነሻውን ፒያሳ ያደረገ አንድ ሰው የዓድዋ ድል መታሰቢያ ጎብኝቶ እንደ አዲስ ከታደሰው በሲኒማ አምፒር የፊልም አምሮቱን ተወጥቶ፣ በራስ ኃይሉ ድልድይ አካባቢ በተሰሩት መናፈሻዎችና የወንዝ ዳርቻዎች ንጹህ አየር ወስዶ ካስፈለገ ጉዞውን ወደ ሽሮ ሜዳ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ካልሆነም በትንሽ ርቀት ላይ ወደሚገኙት አብርሆት ቤተ-መጽሐፍት፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ አንድነት ፓርክ ወይም ብሔራዊ ሙዚየም ጎራ ማለት ይችላል። ስለዚህ ልማቶቹ ሰዎች ከአንዱ አካባቢ ወደ ሌላው በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ አድርገዋል የሚባለውም ለዚሁ ነው። በእርግጥ ይህ ለከተማው ነዋሪ ብቻ ሳይሆን አዲስ አበባ የዲፕሎማቶችና የተለያየ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ለውጭ ሀገር ሰዎችም የምትመች እንድትሆን ያደርጋታል፡፡
በሳህሉ ብርሃኑ