ተምሳሌትነት፣ ለሌሎች መትረፍን፣ ማዘንን በልኩ የምንረዳበት፣ ለነፍስ ሀሴቷ ለስጋም ውበቷ ነው፤ መውሊድ። የመውሊድ በዓል የነብዩ ሙሐመድ የልደት በዓል ነው፡፡ ፍቅር ለማስረፅ፣ ክብራቸውን ለማላቅ፣ ማኅበራዊ ትስስርን ለማጎልበት፣ ለዳዕዋና ለታሊም ጭምር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ በድምቀት እንደሚከበር የኃይማኖቱ ሊቃውንት ይናገራሉ፡፡
መውሊድ ፍቅር ነው፤ መውሊድ አንድነት ነው፤ መውሊድ ከዱኒያ ፍቅር የበለጠ ወደ ፈጣሪ የምንቀርብበት መሰላል ነው ይላሉ ከአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት የዕምነቱ ተከታይ አቶ አህመድ ሰይድ ካሊድ፡፡ በዓሉ አንዳንዴም መውሊድ አል ነቢ፣ ሚላድ፣ ኢድ ሚላድ ኡን ነቢ፣ ኢድ አል-መውሊድ በመባል በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገለፅም አጫውተውናል፡፡
አቡ ዳውድ ኡስማን “ኢስላማዊ እውነታ፤ የአላህን መልዕክተኛ ተወዳጁን ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) በትክክለኛው ማፍቀር!!” በተሰኘ ፅሑፋቸው የእስልምና እምነት ተከታዮች የነብዩ ሙሐመድን ልደት ከማክበር ባለፈ ስብዕናቸውን የዕለት ተዕለት ተግባራቸው ማድረግ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡
በዚህም የነቢዩ ሙሐመድ የህይወት ታሪክንና ፈለግ (ሱና) እንማር። ህይወታቸውን ስናውቀው ይበልጥ እናፈቅራቸዋለን። ፈለጋቸውን ስናነብ ብሎም ተግባራዊም ስናደርግ ይበልጥ እንወዳቸዋለን። የነቢዩ ሙሐመድ ፈለግ እንዲሁ የአንድና የሁለት መፅሐፎች ጥርቅም ሳይሆን የህይወት መስመር ነው። ነብዩ ሙሐመድ የፍቅር መምህር ነበሩ። ሳር ቅጠሉን፣ ጠላት ወዳጃቸውን፣ ዘመድ አዝማዱን፣ የሚያፈቅሩ ድንቅ መምህር ናቸው። ይህን አይነት ስብዕና መላበስ የሚቻለው ደግሞ ስናውቀው ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የመውሊድ በዓል የሚከበረው ለነብዩ ሙሐመድ ክብርና ፍቅር ነው። ምዕመኑ ለነብዩ ያለውን ይህን ፍቅር እርስ በእርሱ ማንፀባረቅ ይኖርበታል። ለነብዩ ሙሐመድ የሚሰጠው ክብርና ፍቅር በሰው ልጆች መካከል መፋቀርና መከባበር እንዲኖር የማድረግ ሚና አለው ይላሉ የእምነቱ ተከታይ አቶ ሙሐመድ ጀማል ፈቂ፡፡
ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉት ሼህ ዘይኑ አደም በበኩላቸው፣ መውሊድ አላህ በነቢዩ ሙሐመድ በኩል ለዓለም የሰጠውን በረከት የምናስብበት በዓል ነው። አንድን ነገር የምንጠብቀው፤ ጠብቀንም የምንጠቀምበት ምን እንዳገኘንና እንዴት እንዳገኘን በሚገባ ካወቅነው ብቻ ነው፤ ይላሉ፡፡
ነቢዩ ሙሐመድ ያደረጉት ነገር ሁሉ ሌሎችን የሰው ልጆች ነጻ የሚያወጣ፣ የሚለውጥና ወደ ተሻለ ሕይወት የሚመራ ነው። ነቢዩን በዚህ ዕለት የምናስታውሳቸው ከአላህ ተልከው ለሰው ልጆች በፈጸሙት መልካም የመልዕክተኛነት አገልግሎታቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ መሐመድ በሽር እንደሚሉት፣ የሰው ልጅ ከባህል፣ ከልማድ፣ ከሞራል፣ ከዝንባሌ፣ ከበዓላት፣ ከአፈ ታሪኮች ከእምነትና ከእሳቤ ጋር የተያያዙ የማኅበራዊ እሴቶቹ ጥገኛ ነው፡፡ በተለይም መንፈሳዊ የሆኑ ማኅበራዊ እሴቶች ከሌሎቹ ከፍ ባለ መልኩ ለሰው ልጅ ለሁለንተናዊ መስተጋብሩ መጠናከር ያላቸው ድርሻና ጉልበት የላቀ ነው፡፡ ከኃይማኖታዊ ትርጓሜያቸው ባሻገር ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ የመገንቢያ ጥበብም ናቸው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩልም መውሊድን የመሳሰሉ ታላላቅ በዓላት እና እሴቶቻቸው የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ መስተጋብር ማጎልበቻ፣ አንዱ አማኝ ጋር ያለውን ወንድማማችነት፣ የአመለካከት አንድነት የሚያንፀባርቅባቸው እንደሆኑም የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ጠቁመዋል፡፡
“ኢስላማዊ እውነታ የአላህን መልዕክተኛ ተወዳጁን ነብይ (ሰ.ዐ.ወ) በትክክለኛው ማፍቀር!!” በተሰኘው የአብዱ ዳውድ ኡስማን ጥንቅር ላይ እንደሰፈረው፣ ነብዩን መውደድ ማለት ሕዝባቸውን (ኡማቸውን) መውደድ ማለትም ጭምር ነው። ለኡማቸው አባላት ጥንቃቄ ልናደርግና ለነርሱም አንድነትና ህብረት ልንሠራ ይገባል። በማንም ሠው ላይ መጥፎ ነገር ልናስብ ወይም ቂም ልንይዝ አይገባም።
ነብዩ ሙሐመድን የወደደ፣ እርሳቸው ያፈቀሩትን ሁሉ ያፈቅራል፤ ያከበሩትን ሁሉ ያከብራል። ነቢዩ ፍጡርን ሁሉ ይወዱና ለነሱም ይሳሱ ነበር። እኛም ለፍጡራን ሁሉ ልንሳሳና ልናዝን ይገባናል። ለአንዳቸውም የጥላቻ መንፈስ በውስጣችን ልናሳድር አይገባም። ሙሐመድ ያፈቅሩትን እኛ ጠልተን እንዴት የሙሐመድ ወዳጅ መሆን እንችላለን? አነስ ኢብኑ ማሊክ ነቢዩ እንዲህ በማለት መከሩኝ ይላል፣ “ልጄ ሆይ! ቀንህንና ምሽትህን ለማንም የጥላቻ መንፈስ ሳይኖርህ ማሳለፍን አትዘንጋ!” ከዚያም እንዲህ አሉኝ፣ “ልጄ ሆይ! ይሄ የኔ ፈለግ ነው፣ ፈለጌን የወደደ በእርግጥ እኔን ወደደ፣ በእርግጥ እኔን የወደደ ከኔ ጋር በጀነት ይሆናል” ማለታቸውንም ምንጭ ጠቅሰው በአስረጂነት ያቀርባሉ።
አክለውም የፍጥረታት መሪው ሙሐመድ የተላኩት ለዓለማት እዝነት ነው። በዓለም ላሉ ፍጥረታት ሁሉ እዝነት። በዚህ ቃል የታነፀ የነቢዩ ወዳጅ በእርግጥ ለሰው ልጅና ለፍጥረታት ሁሉ ያዝናል። ከዚህች ዓለም ላይ ድህነትን፣ ችግርን፣ ሰቆቃንና ረሀብን ለማጥፋት ይጥራል። ሙሐመድ ኢ-ፍትሐዊነትን ለማጥፋት ተልከዋል። ሙሐመድን የሚወድድ ሁሉ ለሰላምና ፍትሕ፣ ለነፃነትና መረጋጋት ዘብ ይቆማል። ሙሐመድ የሰውን ልጅ ከዚያ ከባድ የእሳት ቅጣት ለመታደግ ተልከዋል። የነቢዩ አፍቃሪ ሁሌም ለሰው ልጆች የእውነትንና የስኬትን መንገድ ይሰብካል፤ ብለዋል።
ሼህ ዘይኑ አደም በበኩላቸው፣ የነቢዩን ርህራሄ በሕይወታቸው በመተርጎም የሰው ልጆች ሁሉ በመካከላቸው የሚስተዋሉ አለመስማማቶችንና ግጭቶችን በመተሳሰብና በአብሮነት ለመፍታት ሊተጉ እንደሚገባም የእምነቱ ተከታዮች ተናግረዋል፡፡
ኡስታዝ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር) ነብዩ በሀዲሳቸው ላይ “ያታለለ ከእኛ አይደለም” እንዳሉት በእምነቱ መዋሸት፣ ማታለል ክልክል ነው፡፡ ይህም እቃ በመሸጥም ሆነ በሌሎች ተግባራት የተከለከለ ነው፡፡ ይህም በሌሎች እምነቶች ላይም ይህንን መሰል እሴቶች አሉ፤ እነዚህንም በሚገባ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
ሀቀኛ ብንሆን ከፍታችን ይጨምራል፤ እንደ ሀገርም እንከበራለን ያሉት ኡስታዝ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር) ለአብነትም በእምነቱ ኢትዮጵያ የፍትሕ ሀገር ናት እንደተባለች አስታውሰው፣ ይህ ማለት የእውነት ሀገር ውሸት የሌለባት ማለት ነው፡፡ ሱሀባዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲሄዱ ነብዩ ሲያዙ የፍትሕ ሀገር ብለዋታል። በወቅቱም የኢትዮጵያው መሪ አል ነጃሽ አሳልፈው እንዲሰጧቸው ገንዘብና መሰል ማባበያ አልቀበልም ያሉት ሀቀኛ ስለነበሩ ነው፡፡ በመሆኑም እኛም ይህንን መሰል የአባቶቻችንን ታሪክ መድገም ይኖርብናል። ሁሉም በሀቅ ከሰራ ሀገራችን ትለወጣለች ሲሉም አክለዋል፡፡
ነጋዴው፣ ገበሬው፣ ተማሪው፣ የኃይማኖት አባቶች በሀቅ ቢሰሩ በረከት ይበዛል፤ ሰላም ይነግሳል፡፡ አሁን እኮ ብዙ አይነት አለመግባባቶችና ግጭቶች እየተፈጠሩ ያሉት ፍትሐዊነት ሲጎድል ሀቀኝነት ስለጠፋ ነው፡፡ በመሆኑም ወደ ኃይማኖታዊ እሴቶቻችን ልንመለስ ይገባልም ብለዋል፤ ኡስታዝ ኑረዲን ቃሲም (ዶ/ር )፡፡
አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚው ተሾመ ብርሃኑ ከማል “የመውሊድ ማኅበራዊ ፋይዳ ምንድን ነው?” በተሰኘ ፅሑፋቸው እንደገለፁት፣ የነብዩ ሙሐመድ ልደት፣ መውሊድ በእስልምና ዓለም እጅግ የተከበረ በዓል ነው። በኢስላማዊ የጨረቃ አቆጣጠር ሶስተኛ ወር በሆነው በረቢኡል አወል የሚከበረው ይህ ቀን የነብዩን አርአያ ህይወት እና በሰው ልጆች መካከል ፍቅርና መከባበርን በመንከባከብ የነበራቸውን ሚና በእጅጉ የሚያስታውስበት ነው። ምእመናንም ይህንን የተቀደሰ ቀን ለማክበር ሲሰባሰቡ፣ የነቢዩ ሙሐመድ ትምህርቶች የነበራቸውን ጥልቅ ተፅእኖ ለማሰላሰል እና በማህበረሰቡ ውስጥ የአንድነት እና የርህራሄ ስሜት ማጠናከሪያ ጊዜም ይሆናል።
በመለሰ ተሰጋ