*********************************************************************************************************
በቅርቡ (ማለትም የፈረንጆች 2025 ከገባ በኋላ)፤ ቱርክ፣ ግሪክ እና ቆጵሮስ የታላላቅ ዓለም አቀፍ የዜና አውታሮችን ሽፋን ተቆጣጥረውት እንደነበር ይታወሳል፡፡ የዚህ ምክንያቱ በአገራቱ በተቀራራቢ ጊዜ ውስጥ የተከሰተው የሰደድ እሳት አደጋ ነው፡፡ ይህ አደጋ በሽፋኑም ሆነ ባስከተለው ጉዳት ሲመዘን ትልቅ የሚባል ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ በ“Centre for Environmental Policy at Imperial College in London” የተሠራ ጥናት ውጤት እንዳመለከተው፤ በእነዚህ አገራት በተከሰተው የሰደድ እሳት አደጋ ከ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የመሬት ሽፋን አካልሏል፡፡ በአደጋው 20 ሰዎች ሞተዋል፡፡ ከ80 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ መኖሪያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል፡፡
በእነዚህ አገራት የተከሰተው አደጋ አዲስ አይደለም፡፡ ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከአፍሪካ እስከ እስያ፣ ከአውስትራሊያ እስከ አንታርክቲካ ያለው የምድራችን ክፍል ይህንን መሰል እና ከዚህ የከፋ አደጋን ተጋፍጧል፤ እየተጋፈጠም ይገኛል፡፡
በጎርጎሮሳዊያን የዘመን ቀመር በወርሃ ጥር 2025 ላይ The World Meteorological Organization (WMO) ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ፤ የአየር ንብረት ለውጥ አስከፊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መጥቷል፡፡ ከዓመት በፊት ማለትም በ2024 የተመዘገበው የሙቀት መጠን በከፍተኛነቱ በቀዳሚነት የተመዘገበ ሆኗል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ መሬት ካመነጨችው ከፍተኛ ሙቀት አማቂ ጋዞች ውስጥ ውቂያኖሶች ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወደ ውስጣቸው ወስደዋል፡፡ ይህ ለየብሱ አካል እፎይታን ቢሰጥም የመሬትን 70 ከመቶ የሚሸፍኑት ውሃማ አካላት እና በውስጣቸው ባሉ ስነ ህይወት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጫናን ፈጥሯል፡፡ ይህም የአርክቲክ ባህር በረዶ እንዲቀንስ፣ የግሪንላንድ እና አንታርክቲካ የበረዶ ግግር እና የበረዶ ንጣፍ እንደ ሰም እንዲቀልጥ፣ የውሃማ አካላት ከፍታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል። የዚህ ድምር ውጤትም የአየር ንብረት ለውጥ አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡
ይህ ብቻ አይደለም፤ የዓለምን ውስን ሃብት እና ጥሪት በማውደምም የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከፍተኛ ሆኗል። በጎርጎሮሳዊያን ዘመን ቀመር 2023 ላይ በዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ድረ ገፅ ላይ ይፋ የተደረገው የጥናት ሰነድ እንዳመላከተው የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም ላይ የሚያስከትለው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ እንደ ጥናቱ ከሆነ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ዓለም በሰዓት 16 ሚሊዮን ዶላር ትከስራለች፡፡ ከ2010 እስከ 2019 በነበሩት ዓመታት ውስጥ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዙ አደጋዎች ዓለም የደረሰባት ኢኮኖሚያዊ ጉዳት 1 ነጥብ 3 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ይህ በዚሁ ከቀጠለ የአየር ንብረት ለውጥ በ2050 ዓለምን እስከ 3 ነጥብ 1 ትሪሊየን ዶላር ሊያሳጣት ይችላል። እናም የዓለም መንግስታት እና ሕዝብ አስቸኳይ መፍትሄ ካልሰጠ ህልውናው አደጋ ይደርስበታል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በኢትዮጵያ
የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ የሚፈጥረው አሉታዊ ጫና በፕላኔቷ ያለ የሠው ልጅ ሁሉ የሚጋፈጠው ዕዳ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያም እንደአገር፣ አዲስ አበባም እንደከተማ የዚሁ ተፅዕኖ ተጠቂ መሆናቸው አይቀርም፡፡ እናም ሁሉም ከችግሩ ለመላቀቅ የሚያስችሉ አማራጮችን በተጠናና በተቀናጀ መልኩ መተግበር ግድ ይላቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በሆርቲካልቸር፤ ሁለተኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በአካባቢ የአየር ንብረት አስተዳደር ዘርፍ ያጠኑትና በጉለሌ ዕፅዋት ማዕከል የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተር አቶ መክብብ ማሞን አነጋግረናቸዋል፡፡ እሳቸውም የአየር ንብረት ለውጥን መነሻ ምክንያት፣ የሚያስከትለውን ጉዳት እና የመፍትሄ አማራጮች እንደአገር ብሎም እንደከተማ ካለው ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማስተሳሰር ሙያዊ ሃሳባቸውን አጋርተውናል፡፡
የሆርቲካልቸር ልማት ዳይሬክተሩ በማብራሪያቸው፤ በዓለም አቀፍም ሆነ በአህጉር ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥ ዋና አጀንዳ መሆን ከጀመረ ቆይቷል። ዋናው ዓላማም የዓለምን ሙቀት መጠንን ከ1 ነጥብ 5 ድግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይጨምር ማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ አፍሪካዊ ሚናን ከመወጣት አንፃር እየሠራች ስላለው ሥራ አቶ መክብብ ሲያብራሩ፤ “አፍሪካዊ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ላይ ዋነኛ ተዋናይ የሚያደርግ ኃላፊነት ወስዳ እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች፡፡ ይህ ተሳትፎዋ ደግሞ በስም ብቻ የተቀመጠ ሳይሆን በተግባር በተደገፈ ሥራ የተረጋገጠና በመረጋገጥ ላይ ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ በታዳሽ የኃይል ልማት እና በመሳሰሉት ዘርፎች እያደረገች ያለውን ሰፋፊ እንቅስቃሴ መመልከት ይቻላል፡፡ ግንባታው የተጠናቀቀውን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በማሳያነት ይጠቀሳል። ኢትዮጵያ በዚህ ብቻ አታበቃም። በጥናቶች የተረጋገጡትን እንደአገር ከታዳሽ የኃይል ምንጭ አማራጮች ከ45 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ተጠቅማ ሌሎች መሰል ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ዕውን በማድረግ ተጠቃሚነቷን ታሳድጋለች” ብለዋል፡፡
የአረንጓዴ አሻራ ሥራ ዓለም ከኢትዮጵያ ሊማርበት የሚያስችል ውጤት የታየበት አገር አቀፍ የልማት ንቅናቄ ነው፡፡ የዚህን ግዙፍ ሥራ እንቅስቃሴና ውጤት በተመለከተም ዳይሬክተሩ ሲያስረዱ፤ ከ1900 እስከ 1990 ዓ.ም በነበሩት ዓመታት የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በከፍተኛ መጠን እያሽቆለቆለ የመጣበት ወቅት ነው፡፡ ሠፊ የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን ወደ 3 ነጥብ 7 ከመቶ አካባቢ የወረደበት ሁኔታ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ይሁን እንጂ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ለተከታታይ ዓመታት እንደአገር በተሠሩ ሥራዎች ከፍተኛ የሚባል ውጤት መጥቷል፡፡ የደን ሽፋናችን በአገር አቀፍ ደረጃ ከ23 በመቶ በላይ አድጓል፡፡ የጥምር ግብርና ሥራ እንዲስፋፋ አግዟል፡፡ የውጭ ምንዛሬ ሊያስገኙ የሚችሉ እንደ ቡና፣ ሻይ ቅጠል፣ ፍራፍሬዎች እና መሰል የግብርና ልማት ሥራዎችን አስፋፍቷል፡፡
በተጨማሪም፤ ተፈጥሯዊ ሃብት ላይ መሥራት ሠላምን ለማስፈን እና መልካም አስተዳደርንም ለማረጋገጥ ያግዛል፡፡ በተፈጥሮ መራቆት ምክንያት ሠው ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ይንቀሳቀሳል፤ ይሠፍራል፡፡ ውስን የተፈጥሮ ሃብትን ብዙ ሠው እንዲጠቀም ያስገድዳል። ይህም እስከ ጦርነት የሚደርስ ግጭት መነሻ ይሆናል በማለትም በምሳሌ አስደግፈው አብራርተዋል፡፡
“በከተማ ውስጥ የሚፈጠሩ በካይ ጋዝና ፍሳሾች ተፈጥሮን የመበከል ተፅዕኗቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ያለውን እውነታ ብንመለከት፡- ከጋራዥ፣ ከቆዳ ፋብሪካዎች፣ ከኢንዱስትሪዎች፣ እና ነዳጅ ከሚጠቀሙ ተሸከርካሪዎች የሚወጡ መርዛማ ፈሳሾች እና ጋዞች የከተማዋን ተፈጥሯዊ ይዘት አዛብቶት ቆይቷል፡፡ ወንዞቿ ተበክለው፣ የአረንጓዴ ዕፅዋት ሽፋኗ ተመናምኖ ቆይቷል” በማለት የተናገሩት አቶ መክብብ፤ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እንደ ከተማ የተሠራው ሥራ ተስፋ ሰጪ ውጤት ማምጣቱን በመረጃ አስደግፈው አስረድተዋል፡፡
እንደሳቸው ገለፃ፤ የአረንጓዴ አሻራ ልማት መርሃ ግብር ከመጀመሩ አስቀድሞ የአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ ሽፋን ከ3 በመቶ በታች ነበር፡፡ አሁን ላይ ከ22 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ በአረንጓዴ ልማት ላይ የተሠራው ስራ አግዟል፡፡ ወንዞቻችን በአዲስ አበባ ብቻ የተገደቡ አይደሉም፡፡ በአባ ሳሙኤል አድርገው ወደ አዋሽ ተፋሰስ ይገባሉ፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ብክለት ውስጥ ሆነው በሚያደርጉት ጉዞ ውስጥ ሰፊ የሆነ የሥነ ምህዳር ተፅዕኖ ያሳርፋሉ ማለት ነው፡፡ አሁን ላይ እየተተገበረ ያለው በኪሎ ሜትሮች የሚለካ የወንዝ ዳርቻ ልማት የከተማዋን ተፈጥሯዊ ስነ ምህዳር በማሻሻል ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታወቃል፡፡ በህመም ላይ የነበሩ ወንዞቻችን ሕይወት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም፤ የአረንጓዴ ልማት አሻራ ለሥራ ዕድል ፈጠራም ሁነኛ አማራጭ ሆኗል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ አንድ ካሬ ሜትር የአረንጓዴ ልማት መንከባከብ ከመንግስት 24 ብር ያስገኛል፡፡ የካርቦን ሽያጭ ላይ አገር በስፋት እንድትሳተፍ የሚያስችላትን አቅም ፈጥሮላታል፡፡
የከባቢ አየር ንብረት ለውጥ ላይ እንደአገር ያለንን አዎንታዊ ሚና ለማስቀጠል ጅምር ሥራዎች መጠናከር አለባቸው፡፡ የአረንጓዴ ልማት ሥራው በህብረተሰብ ተሳትፎ በዘላቂነት የሚተገበር መሆን አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ በየደረጃው ያለ አመራር የግንዛቤ ፈጠራ የሚያደርግበት እና የህብረተሰብ ተሳትፎ የሚረጋገጥበት አሠራር መተግበር ይኖርበታል፡፡
እንደ መውጫ
አዲስ አበባ ከተማ ለነዋሪዎቿ በሁሉም መስክ ምቹ እንድትሆን ለማድረግ ሠፊ ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ፡፡ ምቹነቱ ደግሞ ከሕንጻ እና ከመሰረተ ልማት መስፋፋት ጋር የተያያዘ ብቻ አይደለም፡፡ ነዋሪው የሚስበው አየር፣ የሚጠጣው ውሃ፣ የሚመገበው ምግብ፣ የሚንቀሳቀስበት አካባቢ፣ የሚጠቀማቸው መሣሪያዎች … ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ያለቀቁ እንዲሆኑ ጥረት መደረጉን አቶ መክብብ ማሞ አንስተዋል፡፡ በኮሪደር ልማቱ ትኩረት የተደረገባቸው የአረንጓዴ ሥፍራዎች፣ እንደብስክሌት ያሉ የሞተር አልባ ተሽከርካሪዎች የሚጓጓዙበት መንገድ፣ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሠሩ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት ላይ እንዲውሉ መደረጉ፤ በዓለም ላይ ትልቅ አደጋ የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም ጥረቷን እንደሚያሳይ አስረድተዋል፡፡
የመዲናዋ ሁለንተናዊ ለውጥ አካል የሆነው የአየር ንብረት ለውጥ የመቋቋም ጥረት ለሌሎች አገራት በተሞክሮነት የሚወሰድ ነው፡፡ በዚህ አስደናቂ ለውጥ ውስጥ የምትገኘው አዲስ አበባ፤ “ሁለተኛውን ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ሳምንት” ከሰሞኑ አስተናግዳለች፡፡ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ እና በተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ምክትል ዋና ጸሐፊ ኑራ ሀመላዲጂን ጨምሮ ኢትዮጵያዊያንና ከሌሎች አገራት የመጡ ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
በመድረኩ መክፈቻ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ፤ ኢትዮጵያ የአረንጓዴ የኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባች መሆኗን በመጥቀስ፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር፣ ታዳሽ ኃይልና የኮሪደር ልማት በዜጎች ህይወት ተጨባጭ ውጤቶችን እያስመዘገበ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ጉባኤ በተጨማሪ ከጷጉሜን 3 እስከ ጷጉሜን 5 ድረስ 2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤን ታስተናግዳለች። እነዚህ ጉባኤዎች አዲስ አበባ ብሎም ኢትዮጵያ ለጉዳዩ ላሳዩት የተግባር ምላሽ እውቅና የሚሰጥ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
በደረጀ ታደሰ
#Climatechange
#Drought
#Economy