ነብዩ ሙሐመድ የደግነት፣ የይቅርታና የአሳቢነት ትልቅ ምሳሌ ናቸው። እሳቸው ለሰው ልጆች ያላቸው ፍቅርና ሩህሩህነት ከምንም በላይ ነው። ይቅርታን በማስተማርና የተቸገሩትን በመርዳት የታወቁ ናቸው። እንዲሁም ለጎረቤት፣ ለድሃ፣ ለታመሙና ለተቸገሩ ሰዎች ያላቸው አሳቢነት እጅግ የላቀ ነው። ጎረቤት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም እንኳን መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን አስተምረዋል።
የነብዩ ሙሐመድ ሩህሩህነት ከሰው ልጆች አልፎ እንስሳትንም ይጨምራል። በእስልምና አስተምህሮ የእንስሳት መብት የራሱ ስፍራ ያለው ሲሆን፤ ይህ አስተምህሮ የመጣው ከራሳቸው ከነብዩ ነው። እሳቸው እንስሳት በፍትህና በጥንቃቄ መያዝ እንዳለባቸው ያስተማሩ ሲሆን፣ አላስፈላጊ ስቃይ እንዲያዩ ማድረግን አጥብቀው ይከለክላሉ።
ነብዩ ሙሐመድ በእስልምና እምነት ውስጥ በሩህሩህነታቸው የታወቁ ናቸው። ሩህሩህነታቸው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ይንጸባረቃል። ይህን የነብዩ ሙሐመድ ስብእና፣ ለጋስነት፣ መልካምነት፣ ለሰዎችና እንስሳት የነበራቸው ርህራሄ፣ ከጎረቤት ጋር ሊኖር ስለሚገባው መልካም ግንኙነት፣ ወላጅ የሌላቸውን ልጆች ስለማገዝ፣ ስለውለታ ከፋይነት፣ ራስን ብቻ ከመውደድ በመውጣት ለሌሎች ስለማሰብ ያስተማሩትን ትምህርት ከትበው ከያዙ መጽሐፈት ውስጥ “ነብዩ ሙሐመድ የእዝነቱ ነብይ” የተሰኘው ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው በኡስማን ኑሪ ቶፕባሽ ሲሆን በሙኒራ አብዱልመናን ተተርጉሞ በታዋቂው ኡስታዝ ሐሰን ታጁ የአርትኦት ስራ ተሰርቶለታል፡፡
ፍቅር፣ እንክብካቤና ሥነ ምግባር በነብዩ ሙሐመድ ህይወት
ነብዩ ሙሐመድ ለሰው ልጆች የነበራቸው ፍቅር፣ እንክብካቤና ሥነ ምግባር የሚለካው በቃላት ሳይሆን በተግባር ነበር። አላስፈላጊ በሆነ መንገድ የዛፍ ቅርንጫፍ መቆረጥ የለበትም፣ እንስሳትንም በፍትሐዊ መንገድ መያዝና መንከባከብ ይገባል ብለው ያስተምሩ ነበር። ይህ ሃሳብ በመጽሐፉ ገጽ 79 ላይ እንደሚከተለው ሰፍሯል፡፡
“ነብዩ በሥነ ምግባርና ግብረገብነት ፈፅሞ የሚደርስባቸው እንደሌለ ለመቁጠር የሚያዳግቱ ሶሀቦች ተናግረዋል፡፡ ምንጊዜም ፊታቸው በፈገግታና በብርሀን የተሞላ ነበር። እጅግ ንጹህ ልብ ነበራቸው። ምንም ነገር ምድርን እንዲያቆሽሽ አይፈቅዱም”ይላል።
በተጨማሪም ነብዩ እንግዶቻቸውን ራሳቸው ተነስተው ያስተናግዱ ነበር። ከልጅነታቸው ጀምሮም ከኩራት ነፃ የሆኑና ጊዜያቸውንም አቅም ከሌላቸው፣ ደጋፊ ካጡና ከተገፉ የማህበረሰቡ ክፍሎች ጋር ያሳልፉ ነበር፡፡ ነብዩ ለሰዎች ፍቅርና እንክብካቤ በመስጠት፣ የተቸገረን በመጠየቅ፣ በሥነ ምግባር አርዓያ በመሆን ሌሎችን ማስተማራቸውንም መጽሐፉ ያትታል፡፡
ለህጻናት የነበራቸው ፍቅርና እንክብካቤ
ነብዩ ሙሐመድ ለህጻናት መብቶች ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። የወላጆች ኃላፊነት ልጆችን በጥሩ ሥነ ምግባርና በትምህርት ማገዝ እንደሆነ በተደጋጋሚ አስገንዝበዋል። ከዚህ በተጨማሪም ወላጆች በልጆቻቸው መካከል ያለአግባብ ልዩነት ማድረግ እንደሌለባቸው እና ሁሉም ልጆች በእኩል መታየት እንዳለባቸው ያስተምሩ ነበር። ለምሳሌ ልጆቻቸውን በስጦታ ለማስደሰት በሚፈልጉበት ጊዜ እንኳን ሁሉንም በእኩልነት እንዲያዩ ይመክሩ ነበር።
“የእዝነቱ ነብይ” የተሰኘው መጽሐፍም ይህንን መርህ የሚያጠናክሩ ተጨባጭ ታሪኮችን አካትቷል፡፡ መጽሐፉ፣ “ነብዩ ሕጻናትን መርገም ከልክለዋል፡፡ ለሕጻናት ያሳዩአቸው ከነበሩ ፍቅሮችና ርህራሄዎች መካከል ልጅ እናቱ እየሰገደች ካለቀሰ እናቱ ሶላቱን በማሳጠር ልጇን እንድታባብል መፍቀዳቸው አንዱ ማሳያ ነው” ይላል፡፡
ህፃናትን በፈገግታና በስስት እየተመለከቱ እጆቻቸውን አንስተው በማቀፍ ያጫውቷቸው ነበር፡፡ ልጆችን ሰላም ከማለት፣ ለእነርሱ ፍቅርን ከማሳየት እና ከልጆች ጋር ከመጨዋወትና ከመቀላለድ ተቆጥበው አያውቁም በማለት መጽሐፉ ያትታል፡፡
ለድሆችና ለተቸገሩ ሰዎች ያሳዩ የነበረው ደግነት
ነብዩ ሙሐመድ ችግረኞችን የሚቀርቡት በፍቅርና በወዳጅነት ነበር፡፡ ከችግረኞች ጋር ተቀምጠው የመወያየት እና የጓደኝነት ልማድም ነበራቸው። ጉዳይ ሲያጋጥም ከማህበረሰቡ ጋር አንድ ላይ በመሆን የችግረኞችን ሕይወት ይጋሩ ነበር። ይህ ድርጊት ችግረኞች በህብረተሰቡ ውስጥ እንደተከበሩና እኩል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል። በተጨማሪም ችግረኞችን በደግ ቃል በመቀበል፣ በማዳመጥ እና ከጎናቸው በመቆም በወዳጅነት ያጽናኗቸው ነበር።
ነብዩ ሙሐመድ ለችግረኞች የሚሰጠው እርዳታ በዝምታና ያለ ትዕቢት መሆን እንዳለበት ያስተምሩ ነበር። በአክብሮት በመያዝ እና ራሳቸውን እንዳያሳፍሩ በመጠበቅ ፍቅርና ወዳጅነትን በተግባር አሳይተዋል። ከችግረኞች ጋር መመገብ፣ ማውራት እና ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረግ ተግባር ላይ በመሳተፍ ያላቸውን ቅን ፍቅር እና የቅርብ ወዳጅነት ያሳዩ ነበር፡፡ ይህንንም በመጽሐፉ ገጽ 88 ላይ ከሰፈረው ታሪክ መረዳት ይቻላል፡፡
“ነብዩ አንድ ቀን ወደ መስጂድ መጡ። ችግረኞች በአንድ ጎን ተቀምጠዋል። ነብዩ ሙሐመድ በእነሱ በኩል ተቀመጡና መሳቅና ማውራት ያዙ፤ ከዚያም ይህን ተናገሩ፡- ‘ለስደተኛ ድሆች መልካም አቀራረብ ይኑራችሁ፡፡ እነሱ ከሀብታሞች 40 ዓመት ቀድመው ነው ጀነት የሚገቡት። ምክንያቱም ከገንዘብና ከንብረት ላይ የሚደረግ ምርመራ የለባቸውምና፡፡’
ከዛም ነብዩ ይህን ዱአ አደረጉ፡- ‘አላህ ሆይ! ልክ እንደ ድሆች አኑረኝ። እንደነርሱም ግደለኝ፡፡ ከእነርሱ ጋርም ቀስቅሰኝ፡፡’”
መጽሐፉ ላይ እንደሰፈረውና በተለያዩ መዛግብት ላይ እንደተከተበው ነብዩ ሙሐመድ ለችግረኞች ምግብ እና ልብስ በመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊት በራሳቸው እንዲተማመኑ የሚያስችላቸውን እውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ ያግዟቸው ነበር።
ከእንስሳት ጋር በተያያዘ የነብዩ ሙሐመድ ባህሪ
የነብዩ ሙሐመድ አስተምህሮት በእንስሳት ላይ የነበረውን አመለካከት በመሠረታዊነት ቀይሯል። እንስሳት ዝቅ ተደርገው የሚታዩ እና ለሰው ጥቅም ብቻ የሚያገለግሉ ነበሩ። ነብዩ ግን እንደ ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት መታሰብ እንዳለባቸውና መብት እንዳላቸው አስተምረዋል። ነብዩ ለእንስሳት የነበራቸው እንክብካቤና እዝነት “ነብዩ ሙሐመድ የእዝነቱ ነቢይ” መጽሐፍም አጽንኦት ከሰጣቸው ርእሰ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡
በፊት ሰዎች የእንስሳት ፍልሚያ በማዘጋጀት እንዲጎዳዱ እያደረጉ ይዝናኑ ነበር፡፡ ነብዩ ይህን አስቁመዋል፡፡ አውግዘዋልም፡፡
“አንድ ጊዜ እርሳቸው አጥንቱና ቆዳው ብቻ የቀረ ግመል ተመለከቱ። ባለቤቱንም ‘በዚህ ንግግር በማያውቅ እንስሳ ጉዳይ አላህን ፍራ! እስኪራብ አትጠብቅ’ በማለት ምክር ለገሱት” ይላል መጽሐፉ፡፡
መጽሐፉ የነብዩ ተከታዮች የሰጡትን ምስክርነትም አካትቷል፡፡ ከተከታዮቻቸው አንዱ “ከነብያችን ጋር በመሆን በመጓዝ ላይ ነበርን፡፡ እርሳቸው ለጉዳይ ከእኛ ገለል አሉ፡፡ አንዲትን ወፍ ከሁለት ጫጩቶች ጋር ተመለከትን። ጫጩቶቿንም ወሰድንባት፡፡ ወፏ በጭንቅላታችን ላይ ማንዣበብ ያዘች። ነብያችን ወዲያውኑ፡- ‘ማነው ይህቺን ወፍ ጫጩቶቿን በመውሰድ ያበሳጫት? አሁኑኑ ወደ ጎጆዋ መልሱ’ ሲሉ ተቆጡ” በማለት ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡
ይህ የነብዩ አርአያነትና አስተምህሮ በበርካታ ተከታዮቻቸው ዘንድ በጎ ተጽእኖ ያሳደረ እና ለእንስሳትና ፍጡራን እዝነትን ከእርሳቸው እንዲማሩ ያደረገ ነው፡፡ ከነብዩ ተከታዮች አንዱ ለፍጡራን ከነበረው ርህራሄ እና ፍጡራንን ለአላህ ብሎ ከመውደዱ የተነሳ ብዙ አድርጓል። ለምሳሌ፡- በጉዞ ላይ ባለበት ወቅት ደከመውና ከዛፍ ስር ተኛ፤ ሲነቃም ተነስቶ መንገዱን ቀጠለ፡፡ ጥቂት ከተጓዘ በኋላ በተሸከመው ኮረጆ ላይ ከዛፍ ስር የወጡ ጉንዳኖች መኖራቸውን አስተዋለ። ወደመጣበት ቦታ በመመለስም ጉንዳኖቹን ከነበሩበት አስቀመጠ፡፡ ከቤታቸው ሊያርቃቸው አልወደደምና።
ይህም የነብዩ ምሳሌ ምን ያህል በልቡ እንዳሳደረና ህይወታቸውን እንደኖረው ያሳየናል፡፡ ምክንያቱም ነብዩ አጥብቀው ከተናገሯቸው ነገሮች መሀል፡- “እዝነት በልቡ ያለው ሠው ሁሉም አይነት ጥሩነት አለው” የሚለውን ትልቅ ትምህርት በልቡ አኑሮት ነበር፡፡
ለጎረቤት መልካም መሆንን አስመልክተው የሰጧቸው ምክሮች
ነብዩ ሙሐመድ ለጎረቤት መልካም መሆንን በተግባር አሳይተዋል። ከእርሳቸው ታሪኮች እንደምንረዳው፣ ጎረቤቶቻቸው የሌላ እምነት ተከታይ ቢሆኑ እንኳን ያከብሯቸው እና ይረዷቸው ነበር። የጎረቤት መብት በሐይማኖት ልዩነት እንደማይገደብ በተግባር አሳይተዋል። ለዚህ አስረጅ የሚሆኑ ታሪኮችን በመጽሐፉ በገጽ 107 ላይ ተሰንዶ እናገኛለን፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የአቡዘር ታሪክ ነው፡፡ “ነብያችን ከምግቤ ውስጥ ውሀ በርከት አድርጌ እንድጨምር አዘዙኝ፤ ምክንያታቸው ደግሞ ለጎረቤቴ ማካፈል እችል ዘንድ ነው፡፡”
አቡዘር የኢኮኖሚ አቅማቸው ደካማ ከሆኑት የአላህ መልዕክተኛ ሶሐቦች ውስጥ ነው፡፡ በመሆኑም ምግቡን ለማብዛት ያለው አማራጭ ውሀን አብዝቶ መጨመር ብቻ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ድህነት እንኳን ጎረቤትን ላለማገዝ ምክንያት እንደማይሆን ነው፡፡
በአጠቃላይ “ነብዩ ሙሐመድ የእዝነቱ ነብይ” የተሰኘው መጽሐፍ ከላይ ከተጠቀሱት ርእሰ ጉዳዮች በተጨማሪ ስለወንጀለኞችና ምርኮኞች አያያዝ፣ ስለይቅር ባይነት፣ ለጋስነት፣ ሀቀኝነት፣ ታማኝነትና ግብረገብነት፣ ስለ ነብዩ ታማኝነትና ውለታ ከፋይነታቸው ከአስተማሪ ታሪኮች እና ገጠመኞች ጋር ተወዳጅተው የቀረቡበት ነው፡፡
በጊዜው አማረ