ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ታብሌት እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ይዞ ወደ ትምህርት ቤት መግባት እንደማይቻል ትምህርት ሚኒስቴር አሳሰበ።
በተቀመጠው የትምህርት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፤ መስከረም 2 ቀን 2018 ዓ.ም. ትምህርት ቤቶች ክፍት ሆነው መምህራንና ተማሪዎች ውይይት እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
እንዲሁም ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የ2018 የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀመር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴ ለኢዜአ አረጋግጠዋል።
ሁሉም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናትና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመጡ ወላጆች፣ መምህራንና ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን የንቅናቄ ተግባር እንዲቀጥሉ አሳስበዋል።
ለዚህም የትምህርት ቤት ምዝገባን እስከ መጨረሻዋ ቀን ድረስ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
ከ2018 የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች፤ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ታብሌትና በትምህርት ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩና አዋኪ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዳይገቡ በጥብቅ መከልከሉን አስታውቀዋል።