ግዙፍ ሕዝባዊ ፕሮጀክት ያቃና የኅብር ጉዞ

You are currently viewing ግዙፍ ሕዝባዊ ፕሮጀክት ያቃና የኅብር ጉዞ

AMN- ጳጉሜ 02/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያውያንን የዘመናት የአባይ ወንዝ የበይ ተመልካችነት ቁጭት ታሪክ ይቀይር ዘንድ በብዙዎች ዘንድ ተስፋ የተጣለበት ግድብ አሁን ያለበት ደረጃ ለመድረስ ነገሮች ቀላል አልነበሩም።

ሀገርን ከጎበጠችበት ቀና ያደርጋል፤ የህዝቧንም ተጠቃሚነት ያረጋግጣል ተብሎ የተጀመረው ግድብ፤ ብዙ ተግዳሮቶች አጋጥመውት እንደነበር ይታወሳል፡፡ በአምስት አመታት ይጠናቀቃል የተባለው ግድብ አልቆ ሀገር የብስራት ዜናን ሲጠብቅ የግድቡ ግንባታ በብልሹ አሰራር እና በእዳ መዘፈቁ ታወቀ።

የውሀ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ (ዶ/ር) የህብር ውል በተሰኘው በኦቢኤን በተዘጋጀው ዘጋቢ ፊልም ላይ ፕሮጀክቱን በተገቢው መንገድ መምራት እና ማስተዳደር ባለመቻሉ ባለበት እንዲቆም ተገዶ እንደነበር አንስተዋል።

“የመጀመሪያ 6 እና 7 አመት የግድቡ ግንባታ ወደ ፊት ከመቀጠል ይልቅ ባለበት የመቆም አደጋ አጋጥሞት ነበር፤ ግድቡ ባለበት ለመቆም እንኳን መንግስት ካሳ መክፈል የተገደደበት ሁኔታ ላይ ነበርን” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ከጋዜጣ ፕላስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ይህን በሚያጠናክረው ሀሳባቸው፤ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ስለሀይድሮ ኤሌክትሪክ ምንም አይነት ልምድ በሌለው ኮንትራክተር ምክንያት መንግስት 450 ሚሊዮን ዩሮ ካሳ እንዲከፍል ስለመገደዱ ገልጸዋል።

ሆኖም ይህ ሀገራዊ ስብራት በነበረበት እንዳይቀጥል መንግስት በተለይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የወሰዱት እርምጃ ለፕሮጀክቱ በስኬታማነት መጠናቀቅ ወሳኝ እንደነበር ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቱ ከነ ችግሩ ከመቀጠሉ በፊት ቆም ተብሎ ችግሮች እንዲለዩ፣ ከዛም ወደፊት እንዴት መቀጠል እንደሚቻልም የመፍትሄ ሀሳቦች እንዲቀርቡ የሰጡት ውሳኔ ግድቡ ከነበረበት ወገብ አጉባጭ ችግር ተላቆ ለውጤት እንዲበቃ ማስቻሉ ተገልጿል።

የፕሮጀክት አመራር እና አስተዳደሩ ተለውጦ ግድቡ በትክክለኛው ጎዳና መጓዝ ሲጀምር ሌላ ፈተና ሆኖ የነበረው የታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት ይዘውት ብቅ ያሉት ሁለገብ ጫና ነበር።

በዚህ ሂደት ኢትዮጵያ በአለም ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ ከገዛ መሬቷ በሚፈልቀው ውሀ አጠቃቀም ዙሪያ በጸጥታው ምክር ቤት ተከሳ ምላሽ ለመስጠት ተገዳለች።

የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) እንደሚሉት በኢትዮጵያ ላይ የተነዛው የተበድያለሁ ሀሰተኛ መረጃ ስርጭት እና የዲፕሎማሲ ጫና ያስከተለው ተጽእኖ ቀላል አልነበረም።

በተለይም መንግስት ግንባታው ላይ ብቻ እንዳያተኩር እና በተለያዩ መንገዶች የሚገኙ የገንዘብ ድጋፎች እንዲቋረጡ ምክንያት እንደነበርም ገልጸዋል። መንግስት እነዚህን የሚታዩ እና የማይታዩ ስውር እጆች ለመመከት በሚያደርገው ጥረት ከህዝብ ድጋፍ እና አብሮነት ጋር ተዳምሮ ተጽዕኖዎችን መቋቋም ችሏል።

የትውልድ ቅብብሎሽ፣ ትልም፣ ፍላጎት እና አፈጻጸም እንደሆነ የሚነገርለት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንደወንዙ ቅኔ ነው። ከሲሚንቶ እና ብረት ተሻግሮ በደም ፣ ላብ እና እንባ የቆመው ፕሮጀክት እውን ለመሆኑ የህይወት መስዕዋትነት ጭምር ተከፍሎለታል። ዛሬ ኢትዮጵያ እንደከዚህ ቀደሙ መንገድ ለመገንባት እና ፋብሪካ ለማቆም የአበዳሪዎችን እጅ ብቻ የማትጠባበቅ ሀገር መሆኗን አሳይታበታለች።

ዛሬ ከኢትዮጵያ ጋር መወዳጀት እና በጋራ መስራት ምን አይነት ትሩፋትን ሊያስገኝ እንደሚችል፤ ዜጎቿም በአንድነት ሲቆሙ የሚያስቆማቸው ምድራዊ ሀይል እንደሌለ እነሆ በጉባ ተራራ ህያው ማሳያ ሀውልት ቆሟል።

ታዲያ አሁን ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ14 አመታት ውጣ ውረድ እና ፈተናዎች በኋላ ሊሞሸር ሲሆን በሕብር በፅናት የገነቡትን ኢትዮጵያውያንንም እንደሚክስ እምነት ተጥሎበታል፡፡

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review