የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀጣይ የልማት ሥራ እንዲሸጋገሩ ያደርጋል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ የሕዳሴ ግድብ ምረቃ አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በዚህም ለዘመናት ኢትዮጵያን ቋሚ አድርገው ካቆዩ አምዶች መካከል “ፈለገ ግዮን” የተባለው የዓባይ ወንዝ አንዱ መሆኑን አውስተዋል።

በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የኢትዮጵያ ትዕምርት ተደርጎ የተጠቀሰው የዓባይ ወንዝ በዚህ ዘመን ለሕዝቡ ብርሃን እያበራ አገልግሎት መስጠት የሚችልበት ሁኔታ በመፈጠሩም ፈጣሪን እናመሰግናለን ብለዋል።
የዛሬዋን ቀን በመናፈቅ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ዕለት አንስቶ ለሰሩና ታሪክ በመልካም የሚያስታውሰውን ዋጋ ለከፈሉ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ኢትዮጵያውያን ወደ ቀጣይ የልማት ሥራ እንዲሸጋገሩ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ዘላቂ ሰላም እና ልማት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ነው ያመለከቱት።