ፖላንድ በዛሬው ዕለት የአየር ክልሏ ውስጥ የገቡ የሩስያ ድሮኖችን በኔቶ አጋር ሀገራት ወታደራዊ አውሮፕላኖች ድጋፍ መትታ መጣሏን አስታውቃለች።
ሞስኮ በዩክሬን ላይ በፈጸመችው መጠነ ሰፊ ጥቃት ድንበር አልፈው ፖላንድ ውስጥ የገቡ ድሮኖችን ነው መታ የጣለችው ።
እነዚህን ድሮኖች በመምታት ሂደት ውስጥ አሜሪካን ጨምሮ ሌሎች የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ አባላት አየር ሀይሎች ተሳትፈዋል።
ይህን ተከትሎ የሩስያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የኔቶ አባል ሀገራት በቀጥታ የተሳተፉበት የመጀመሪያው ጥቃት ሆኖ ተመዝግቧል ።
በዛሬው የድሮን ጥቃት ከዩክሬን አቅጣጫ የመጡ 19 አጥፍቶ ጠፊ ድሮኖች የፖላንድን የአየር ክልል ጥሰው መግባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል ።
ከዚህ ቀደም የሩሲያ ሮኬት እና ሚሳኤሎች የአየር ክልሏን በመጣስ ስጋት እየፈጠሩ እንደሚገኙ ዋርሳው በተደጋጋሚ ቅሬታዋን አቅርባለች ።
በአሁኑ ወቅት በፖላንድ የሚገኙ አየር መንገዶች በጊዜያዊነት ስራ እንዲያቆሙ ተገደዋል።
የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ተስክ ለፓርላማ ባደረጉት ንግግር ይህ አጋጣሚ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ለግልጽ ግጭት እጅግ የቀረብንበት ነው ብለዋል።
ያም ሆኖ ከሩስያ ጋር ወደ ሙሉ ጦርነት የሚያስገባ ስጋት እንደሌለባቸው የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ “አንቀጽ 4” የተባለውን በኔቶ አባል ሀገራት ላይ ስጋት ሲያንዣብብ ምክክር እንዲደረግ በሚጠይቀው አንቀጽ መሠረት ለውይይት ጥሪ አቅርበዋል።
ኔቶ ክስተቱን እንደ ቀጥተኛ ጥቃት ባይፈርጀውም ሆን ተብሎ የተደረገ “ሰርጎ ገብነት” ሲል ጠርቶታል ።
ይህን ተከትሎም ሁነቱ በምስራቅ አውሮፓ ያለውን ውጥረት ይበልጥ ስጋት ውስጥ እንደሚከት አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው ።
በዳዊት በሪሁን