የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቭ ህፃናት ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ከማስቻሉም በላይ እናቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲያሳድጉ እድል የሚሰጥ መሆኑ ተገለፀ

You are currently viewing የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቭ ህፃናት ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ከማስቻሉም በላይ እናቶች በኢኮኖሚ እራሳቸውን እንዲያሳድጉ እድል የሚሰጥ መሆኑ ተገለፀ

AMN – ጳጉሜን 5/2017 ዓ.ም

የቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቭ የነገ ሐገር ተረካቢ ህፃናት በአካል፣ በአዕምሮና በስነ ልቦና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ ከማስቻሉም በላይ፤ እናቶች እራሳቸውን በኢኮኖሚ እንዲያሳድጉ እድል የሚሰጥ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ “ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን እናድርግ” በሚል መሪ ሐሳብ እየተከበረ የሚገኘውን ጳጉሜን አምስት የነገ ቀንን ምክንያት በማድረግ በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በመንግስት ወጪ የተገነቡ 17 የህዝብ የህፃናት ማቆያ ማዕከላትን ለአገልግሎት ክፍት አድርጓል፡፡

አዲስ አበባ ከተማን በአፍሪካ ለህፃናት ምቹ ከተማ ለማድረግ ከሚከናወኑ አበይት ተግባራት መካከል ይመደባል- ቀዳማይ ልጅነት ኢኒሼቲቭ፡፡ ኢኒሼቲቩ በይፋ ከተበሰረ እለት አንስቶ መዲናዋ መጪውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ ትላልቅ የልማት ስራዎችን እያከናወነች ትገኛለች፡፡

ይህም የነገ ሐገር ተረካቢ የሆኑ ህፃናት በአካል፣ በአዕምሮና ስነ ልቦና ጤናማ ሆነው እንዲያድጉ እያስቻለም ነው፡፡ ህፃናቱም በውስጣቸው ትላልቅ ራዕይ ሰንቀው እንዲያድጉም በር ከፍቷል፡፡

ለዚህም የሚረዱ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር አንፃር በርካታ ተግባራት በከተማዋ እየተከናወኑ ሲሆን፣ የነገ ቀን በሚል ስያሜ ያገኘውን ጳጉሜን 5 ቀን ምክንያት በማድረግም በመንግስት ወጪ የተገነቡ 17 የህዝብ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ተመርቀዋል፡፡

ጳጉሜን 5 የነገ ቀንን በጉለሌ ክፍለ ከተማ የተለያዩ ኩነቶችን በማዘጋጀት ያከበረው የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ፤ የተመረቁት የህዝብ የህፃናት ማቆያ ማዕከላት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆችን ታሳቢ በማድረግ መገንባቱን አስታውቋል፡፡

በየአካባው የሚሰሩ የልማት ስራዎች ዘመን ተሻጋሪ እና ለመጪው ትውልድ የሚያግዙ ናቸው፤ ለዚህም ሌላው ትልቁ ማሳያ የህዳሴ ግድቡ መጠናቀቅ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ገልፀዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ትኩረት በሰጠው የነገ ሐገር ተረካቢ በሆኑ ሕጻናት ላይ የሚሰሩ ተግባራትን በክፍለ ከተማቸውም እያስቀጠሉ ብቁ ዜጋን የማፍራቱን ሂደት ተጠናክሮ መቀጠሉን የነገሩን ደግሞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ ናቸው፡፡

ዝቅተኛውን የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ የህፃናት ማቆያ ስፍራዎች በአቅራቢያቸው መዘጋጀታቸው እንዳስደሰታቸው የማቆያ ማዕከላቱ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡

የነገው ቀንን ምክንያት በማድረግም በጉለሌ ክፍለ ከተማ በተሰሩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች ላይ ከሚጫወቱ ህፃናት ጋር ስፖርታዊ እንቅስቃሴን በጋራ የማከናወን እና ለታዳጊዎቹ የስፖርት ትጥቅ ድጋፍ የማካሄድ መርሃ ግብርም ተካሂዷል፡፡

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review