የኢትዮጵያን የነገ እግርኳስ የመቀየር አቅም ያላቸው ሜዳዎች

You are currently viewing የኢትዮጵያን የነገ እግርኳስ የመቀየር አቅም ያላቸው ሜዳዎች

AMN – ጳጉሜ 5/2017 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውጤት ባጣ ጊዜ ተደጋግሞ የሚነገር ሀረግ አለ፤ ’’ታዳጊዎች ላይ መስራት አለብን’’ የሚል፡፡

የነገን የኢትዮጵያን ስፖርት ለመቀየር ታዳጊዎች ላይ መስራት ትልቅ መሰረት ነው፡፡ ታዳጊ ላይ ለመስራት ግን በርካታ ግብዓቶች ያስፈልጋሉ፤ በተለይ መጫወቻ ሜዳ፡፡

አዲስ አበባ ድሮ የነበሯትን ሜዳ ቅርጥፍ አድርጋ እየበላች ታዳጊዎች በመጫወቻ ሜዳ እጦት ሲንከራተቱ ተመልክተናል፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ለእግርኳሱ እድገት መሰረት በሆነው ታዳጊ ላይ ስለመስራት ማውራት ከባድ ነበር፡፡

አሁን ነገሮች በብዙ ተቀይረዋል፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት ሜዳዎች እንዲገነቡ በልዩ ትኩረት መስራቱ ለታዳጊዎች ትልቅ ብስራት ሆኗል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ካመጣቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች አንዱ የሜዳዎች በብዛት መሰራት ነው፡፡ በየሰፈሩ የተሰሩ ሜዳዎች የህፃናት እና ታዳጊዎች መቦረቂያ መሆን ችለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) እነዚህ ሜዳዎች ለነገ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ማንሰራራት ምክንያት የመሆን አቅም እንዳላቸው ያምናሉ፡፡

እግር ኳስን የሚወዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ቡድኑ ሁል ጊዜ እንደተቆጩ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ መቆጨት ብቻ ምንም ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ፡፡

ከመቆጨት በዘለለ እግርኳሱ የሚፈልገው ግብዓት ላይ ፈሰስ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አብራርተዋል፡፡ መንግስት በየሰፈሩ ሜዳዎች እንዲገነቡ ያደረገውም የወደፊቱን ውጤት በማሰብ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በአዲስ አበባ የተገነቡ በሺ የሚቆጠሩ ሜዳዎች ቢያንስ አንድ አንድ ተጫዋች ማፍራት ቢችሉ ትልቅ ስኬት ነው የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ታዳጊዎች ላይ በምንሰራው ስራ ብሄራዊ ቡድኑ እንዲያንሰራራ ማድረግ እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ብቸኛ ስኬቱ የ3ኛው አፍሪካ ዋንጫ ድል ነው፡፡ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን ከመሰረቱ ሀገራት አንዷ ለሆነች ሀገር ውጤቱ የሚገባ አይደለም፡፡

የመንግስት ትኩረት ታክሎበት ሳይንሱን በተከተለ መንገድ ከተሰራ ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ለዚህ ከሚያስፈልጉ ግብዓቶች አንዱ ሜዳ ነው፡፡

በአዲስ አበባ እየተገነቡ የሚገኙት ሜዳዎች ለታዳጊዎች መቦረቂያ ብቻ ሳይሆን፤ ለነገ የኢትዮጵያ እግርኳስ እድገት ምክንያት የመሆን አቅም እንዳላቸው ይታመናል፡፡

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review