በመዲናዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በክፍለ ከተሞች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

You are currently viewing በመዲናዋ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎትን በክፍለ ከተሞች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል

AMN ጳጉሜን 5/2017

በመዲናዋ ቀልጣፋ አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በክፍለ ከተሞች የማስፋት ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር(ዶ/ር) ገለጹ፡።

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

የከተማዋ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ቢሮ ሀላፊ ጀማሉ ጀምበር(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የመዲናዋን ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሰፋፊ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡

ከአገልግሎት አሰጣጥ አንጻርም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን ነው ያነሱት።

ሆኖም አንዳንድ አገልግሎቶች በተበታተነ መልኩ ሲሰጡ መቆየታቸው እንዲሁም ተመሳሳይ አገልግሎቶችን ለማግኘት ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም መሄድ የመልካም አስተዳደር ችግር ሲፈጥር መቆየቱን አስታውሰዋል።

ይህንን ችግር በመሰረታዊነት ለመፍታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አቅጣጫ ሰጪነት የተጀመረው የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት በአዲስ አበባ ወደ ሥራ መግባቱን ተናግረዋል፡፡

አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተቋማት በአንድ ሥፍራ በቴክኖሎጂ ተሳስረው እንዲሰሩ በማድረግ አገልግሎትን ያሳልጣል ነው ያሉት።

በአዲስ አበባ አራዳ ክፍለ ከተማ የተጀመረው የአንድ ማዕከል አገልግሎት 13 ተቋማት አገልግሎት የሚሰጡ መሆኑን አስታውቀዋል።

ይህ በአንድ ጊዜ ለበርካታ ተገልጋዮች በተቀላጠፈ ሁኔታ አገልግሎት በመስጠት ዜጎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግና የመልካም አስተዳደር ችግርን እንደሚያቃልል ጠቁመዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱን የማስፋት ስራ ተጠናክሮ አንስተውም በቅርቡ በቦሌ ክፍለ ከተማ መጀመር የሚያስችል ስራ እየተጠናቀቀ ነው ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በ2018 ዓ.ም ሁሉም ክፍለ ከተሞች የአንድ ማዕከል አገልግሎት እንዲጀምሩ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review