ከቀድሞው አስጊ ህይወት ተላቅቀው በዓሉን በደስታና በአዲስ መንፈስ ለማክበር መዘጋጀታቸውን የልማት ተነሺዎች ተናግረዋል
አዲስ አበባን አቋርጠው በሚያልፉ ወንዞች ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ኑሯቸው ከዕለት ተዕለት ችግር ጋር ትግል ነው። የክረምት ወቅት ሲመጣ፣ የጎርፍ አደጋ ፍራቻ ከመጠን በላይ በመጨመር የነዋሪዎች እንቅልፍ ማጣት ሳያንስ ቤቶች በጎርፍ ሲወሰዱ፣ ንብረት ሲወድም እና ህይወት በከንቱ ሲጠፋ መመልከት የተለመደ ነበር፡፡ ይህ አሰቃቂ ሁኔታ በወንዝ ዳርቻ ልማት አማካኝነት ታሪክ ከመሆኑ በፊት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ 19 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ መሰረት ጉደታም ህይወት ይኸው ነበር፡፡
በእርግጥ አሁን ላይ ልክ እንደ ወይዘሮ መሰረት ሁሉ በአዲስ አበባ በወንዞች አካባቢ ይኖሩ የነበሩና አሁን ወደተሻለ መኖሪያ ቤት የተዛወሩ ነዋሪዎች የሕይወት ለውጥ አስደናቂ ታሪክ አለው። ቤታቸውን እና ኑሮአቸውን ከወንዙ ጎርፍ ጋር ሲያፈራርቁ ከኖሩበት አስጨናቂ ትዝታ የሞላበት ህይወት፣ ወደ ዘመናዊ እና የተረጋጋ ኑሮ ተሸጋግረው አዲስ ዓመትን በአዲስ መንፈስ ለመቀበል ተዘጋጅተዋል። ይህ ለውጥ ታዲያ ከግለሰብ አልፎ የህብረተሰብ እና የአንድ ከተማ ዕድገት መገለጫ እንደሆነ እንረዳለን።
ወይዘሮ መሰረት በእድሜ ከገፉ ጡረተኛ ባለቤታቸው ጋር በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ለዘመናት በስጋት ኖረዋል። የወንዝ ሙላት ከአሁን አሁን ወሰደን በማለት ከእነቤተሰቦቻቸው የሰቀቀን ኑሯቸውን ገፍተዋል፡፡ ወደ ወንዙ የመጸዳጃ ቤት ፍሳሽና የተለያየ ቆሻሻ ስለሚለቀቅበት ሽታው የአካባቢውን ነዋሪዎች በመረበሽ የጤና መስተጓጎል አስከትሎባቸው ነበር። ለአስም እና ለሌሎች የመተንፈሻ አካላት ህመም ተጋላጭ ነበሩ፡፡ በሌላ በኩልም የወንዙ ድምጽ ዘወትር እረፍት ነስቷቸው እንደነበር በምሬትና በትካዜ ያስታውሳሉ። በፊት ይኖሩበት የነበረው አካባቢ የወንዝ ዳር በመሆኑ ልጆችን ለማሳደግ እና ለመኖሪያነት እንደማይመች ገልጸው፣ አሁን የሚኖሩበት አካባቢ ለኑሮ ምቹ መሆኑን ወይዘሮዋ ያስረዳሉ፡፡
በልማት ምክንያት በስጋት ከሚኖሩበት የወንዝ አካባቢ ተነስተው ከአካባቢያቸው ሳይርቁ በጉለሌ ወረዳ 1 ሽሮ ሜዳ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ጀርባ ‘ምንታምር የጋራ መኖሪያ ሳይት‘ የመኖሪያ ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ የተሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤት ለኑሮ የተመቻቸ እና መሰረተ ልማት የተሟላለት አካባቢ መሆኑን ወይዘሮ መሰረት ያብራራሉ፡፡
ዛሬ ላይ ወይዘሮ መሰረት እና ጓደኞቻቸው ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ሳይለቁ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ በአንድ የጋራ መኖሪያ ህንጻ ይኖራሉ፡፡ ልክ እንደ ወይዘሮ መሰረት ሁሉ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ሰዎች ከጎረቤቶቻቸው ጋር የቀደመው ማህበራዊ ግንኙነታቸው ሳይቋረጥ በዓሉን በደስታ ለማክበር ተዘጋጅተናል ይላሉ፡፡ ከአንድ አካባቢ የተነሱ የልማት ተነሺዎች በጋራ መኖሪያ ስፍራ ማህበራዊ ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንደ እድር፣ እቁብ፣ ማህበር መስርተዋል። የግቢው ነዋሪዎች ችግራቸውን፣ ሀዘናቸውን እና
ደስታቸውን በጋራ ይካፈላሉ፤ በዓልን በአብሮነት ስሜት በጋራ ያሳልፋሉ፡፡
በወንዝ ዳርቻ ልማት ምክንያት ከአንድ አካባቢ ተነስተው፤ ሳይነጣጠሉ ከነበሩበት ቀያቸው ብዙም ሳይርቁ በአንድ የጋራ መኖሪያ አካባቢ ቤት ማግኘታቸው ማህበራዊ ኑሯቸው ሳይናጋ ህይወታቸውን እንዲያስቀጥሉ እንዳስቻላቸው ወይዘሮ መሰረት ተናግረዋል፡፡ በአዲስ ቤት በዓል ማክበር የተለየ ስሜት ይፈጥራል የሚሉት ወ/ሮ መሰረት በዓልን ከባለቤታቸው እና ከጎረቤታቸው ጋር በደስታ ለማሳለፍ ቅድመ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
የዘመን መለወጫ በዓልን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ቤት ያፈራውን በልተው እና ጠጥተው በጋራ እንደሚያሳልፉ ወይዘሮ መሰረት ገልጸው፣ አሁን አዲሱን ዓመት በአዲስ ቤት ማሳለፋቸው ድርብ በዓል ያደርገዋል ይላሉ፡፡ በዚህም ደስተኛ ሆነው ከቤተሰቦቻቸው እና ከጎረቤታቸው ጋር በጋራ የዘመን መለወጫ በዓሉን እንደሚያሳልፉ ገልጸዋል፡፡
ወይዘሮ ሐረገወይን አስገዶም በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ መነን የሚባል አካባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፣ በአፍንጮ በር አካባቢ በሚሰራው የወንዝ ዳርቻ ልማት ምክንያት ከአካባቢያቸው ተነስተዋል፡፡ ከበፊት አካባቢያቸው ሳይርቁ በሽሮ ሜዳ ምንታምር የጋራ መኖሪያ ሳይት ቤት ተሰጥቷቸዋል፡፡ አምስት ቤተሰቦችን የሚያስተዳድሩት ወ/ሮ ሀረገወይን በፊት ይኖሩበት የነበረው ቤት ልጆችን ለማሳደግ አካባቢው የማይመች እንደነበር አንስተዋል፡፡ የውሃ እና የመጸዳጃ ቤት እጥረት ፈተና ሆኖባቸው እንደነበር ወይዘሮ ሀረገወይን ገልጸው፣ በአዲሱ ቤት ይህ እጥረት መቀረፉን ያስረዳሉ፡፡
ወይዘሮ ሐረገወይን በተለይም ለብዙ ጊዜ አብረው የኖሩ እና የሚተዋወቁት ጎረቤቶቻቸው
ጋር በአንድ አካባቢ መሆናቸው ከምንም በላይ እንዳስደሰታቸው ያነሳሉ። የመኖሪያ አካባቢው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ተስማሚ መሆኑን አንስተው፣ መሐል ከተማ ላይ ከአካባቢያቸው ብዙም ሳይርቁ ምትክ ቤት በማግኘታቸው ለዘመናት አብረው የኖሩ ጎረቤቶች በአንድ አካባቢ መሆናቸው ሀዘንና ደስታቸውን በጋራ ለመካፈል አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአንድ አካባቢ ይኖሩ የነበሩት እማወራ እና አባወራዎች በልማት ሲነሱ በአዲሱ የመኖሪያ ሰፈር በጋራ በአንድ አካባቢ በመሆናቸው በፊት የነበሩትን የማህበራዊ ህይወት እና ግንኙነቶችን ማስቀጠላቸውን ገልፀዋል፡፡ በመኖሪያ አካበቢው እንደ እድር፣ እቁብ፣ ማህበር ያሉ ማህበራዊ ጉዳይን የሚያጠናክሩ ግንኙነቶችን አስቀጥለዋል፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በበዓል ወቅት ሲሆን ትርጉሙ ብዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የዘመን መለወጫ በዓልን ቤት ያፈራውን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ተካፍለው በደስታ እንደሚያሳልፉ የሚናገሩት ወይዘሮ ሀረገወይን፣ ለበዓል ዝግጅት ለጠላ እና እንጀራ ግብዓት የሚሆን እህል ከወዲሁ በመግዛት ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል። በአቅማቸው ቤታቸው ያፈራውን ከጎረቤታቸው ጋር ተባብረው በዓልን በጋራ ለማሳለፍ ከወዲሁ ዝግጅት አድርገዋል፡፡
ወይዘሮ ሐረገወይን ቡና በጋራ መጠጣት አንዱ የማህበራዊ ኑሮ መገለጫ መሆኑን አንስተው፣ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ ቡና ይጠጣሉ፤ ስለ አብሮነት ህይወታቸው በጋራ ይመክራሉ። ማህበራዊ ኑሮን ለማጎልበትም ሆነ ደግና ክፉ አጋጣሚዎችን በጋራ ለመወጣት መሰረቱ ጉርብትና ነው። ለልማት ተነስተው ምትክ በተሰጣቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እድርና መሰል የማህበራዊ ህይወት እየቀጠለ ነው፡፡
ከፒኮክ መናፈሻ አካባቢ በልማት ምክንያት ምትክ የተሰጣቸው መቶ አለቃ ሀይረዲን አሊ እንደዚሁ በምንታምር ሳይት የጋራ መኖሪያ ቤት ይኖራሉ። አሁን ላይ የእነ ወይዘሮ መሰረት እና ወይዘሮ ሀረገወይን ጎረቤት ናቸው፡፡ በአዲሱ የጋራ መኖሪያ ቤት ማህበራዊ ግንኙነቶች የቀጠሉ መሆኑን አንስተው ከጎረቤቶቻቸው ጋር በችግር፣ በሃዘን፣ በደስታ የጋራ ተካፋይ ናቸው፡፡ ከጎረቤቶቻቸው ጋር ደስታቸውን እና ችግሮቻቸውን በጋራ ተጋርተው የሚኖሩት እነ መቶ አለቃ ሀይረዲን በመተሳሰብ፣ በፍቅር እና በሰላም በአንድነት ይኖራሉ፡፡ ማህበራዊ ችግሮች ሲያጋጥማቸው በጋራ የሚሳልፉት ጎረቤታሞቹ በዓል ሲደርስም ያለው ለሌለው በማካፈል እና በጋራ ማዕድ በማጋራት ያሳልፋሉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሶፎንያስ ፍስሐ የክረምት በጎ ፈቃድ ከግንቦት እስከ መስከረም 30 በተለያዩ መርሃ ግብሮች ተግባራዊ እየሆነ መሆኑን ተናግረዋል። አቶ ሶፎኒያስ በዚህ ዓመት ቤት ማደስ ብቻ ሳይሆን የግንባታ መርሃ ግብር የተያዘ ሲሆን፣ ቤቶችን ባሉበት አፍርሶ መልሶ የመገንባት ፕሮግራም ተይዞ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በቤት ግንባታ መርሃ ግብርም ከ2 ሺህ 400 በላይ ቤቶችን በአዲስ እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል። በግንባታ ሂደት ላይ ካሉ ቤቶች መካከል አብዛኞቹ ተጠናቅቀው ለአዲሱ ዓመት ለነዋሪዎች የሚተላለፍ መሆናቸውን አቶ ሶፎኒያስ ጠቁመዋል፡፡
በከተማዋ ዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍል የሚኖርባቸው ቤቶች በበጋ ጊዜ ነፋስ፣ ጸሐይ በክረምት ደግሞ ጣሪያቸው የዝናብ ፍሳሽ በማስገባት ለጎርፍ ተጋላጭ የነበሩ እና ለኑሮ የማይመቹ ቤቶችን አፍርሰው በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በከተማዋ የሚገኙ የተለያዩ ባለሃብቶችን እና በጎ ፈቃደኞችን በማሳተፍ የቤት መገንባት ፕሮግራም እየተከናወነ ሲሆን፣ ቤታቸው ባለበት ፍርሶ ሳይርቁ ቤታቸው እየተገነባ ነው፡፡
አዲስ የሚገነቡ ቤቶች በአነስተኛ ወጪ የሚገነቡ ባለ አንድ ወለል እና ከዚያ በላይ የሆኑ ቤቶች ናቸው፡፡ እነዚህም ቤቶች የራሳቸው መታጠቢያ ቤት፣ ማብሰያ ክፍል፣ መኝታ ቤት የተሟላላቸው ሲሆኑ፣ ነዋሪዎቹ በፊት ሲኖሩባቸው ከነበሩባቸው ቤቶች በጣም በተሻለ ሁኔታ ንጽህናው የተጠበቀ፣ ለመኖሪያ ያማረ ምቹ አካባቢ እየተፈጠረ መሆኑን አቶ ሶፎኒያስ ተናግረዋል፡፡ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታም ለነዋሪዎቹ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ ልቦናዊ ጠቀሜታ ያላቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ አብረዋቸው ለረጅም ጊዜ ከኖሩ እና ከሚያውቁት ጎረቤት ሰዎች ጋር አብረው መሆናቸውም የእርስ በእርስ ግንኙነቶች እና መስተጋብር ይበልጥ እየተጠናከረ ስለሚሄድ ማህበራዊ ህይወት እንዲቀጥል የሚያደርግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሽሮሜዳ አካባቢ በሚገኘው በምንታምር ሳይት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ በልማት ምክንያት የተነሱ 210 አባወራ እና እማወራዎች በጋራ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ነዋሪዎች ማህበራዊ ግንኙነታቸውን ማስቀጠላቸውን በአካል ተገኝተን ለማረጋገጥ ችለናል፡፡
በይግለጡ ጓዴ
#Volnteerism
#Addis Ababa