ከግድቡ ግንባታ ጅማሮ ያለማቋረጥ ድጋፍ ያደረጉት አስር አለቃ ኃይለማርያም አለሙ
ዓባይ የሚጠበቅበት ብዙ ቢሆንም ትሩፋቱ ግን ምንም፣ አለፍ ሲልም ጉዳት ሆኖ ለዘመናት ቆይቷል፡፡ “ዓባይ ማደሪያ የለው ግንድ ይዞ ይዞራል…” የመባሉ ምክንያትም ይኸው ነው፡፡ ይህን የቁጭትና አለመቻል ታሪክን የመቀየር ትልም መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሰረተ ድንጋይ ሲጣል ተጀመረ፡፡ የግድቡ ግንባታ መጀመር ኢትዮጵያውያን ለአንድ ዓላማ በአንድ ልብ እንዲሰለፉ አደረገ፡፡
በራስ አቅም ለመገንባት የተያዘውን፣ የዘመናት እንቆቅልሽ የሚፈታውን ይህን ታላቅ ግድብ እውን ለማድረግ ከህፃን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ አነስተኛ ሸቀጣ ሸቀጥ እየነገዱ ከሚተዳደሩ እስከ ዲያስፖራው ድረስ እጃቸውን ለመቀበል ሳይሆን ለመስጠት ዘረጉ፡፡ የአንድነት አርማ ለሆነው ግድብ ከተረፋቸው ሳይሆን ካላቸው በማካፈል መቀነታቸውን እየፈቱ፣ ከኪሳቸው ሽርፍራፊ ሳንቲም እያዋጡ ታሪክ ለመስራት ተሽቀዳደሙ፡፡
የግድቡ ግንባታ ከተጀመረ በኋላ ቀናት፣ ዓመታት ተቆጥረው በመጨረሻም ግድቡ የአዲስ ዓመቱ ታላቁ ስጦታ ሆናል። በዚህ ጉዞ ከጅምሩ አንስቶ ለግድቡ ያለማቋረጥ ድጋፍ ሲያደርጉና ፍጻሜውን ለማየት ከጓጉት ኢትዮጵያውያን መካከል አስር አለቃ ኃይለማርያም አለሙ አንዱ ናቸው፡፡
የህዳሴው ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ከመጣሉ አስቀድሞ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን ለዘጠኝ ዓመት ያህል ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አስር አለቃ ኃይለማርያም ሀገራቸውን በሚያገለግሉበት ወቅት በደረሰባቸው ጉዳት በጡረታ ለመውጣት ተገደዱ። በመከላከያ ሰራዊት ብዙ ዓመት ሀገራቸውን ማገልገል ቢፈልጉም በጉዳታቸው ምክንያት መቀጠል አለመቻላቸው ቁጭት ፈጥሮባቸው ቆይቷል፡፡
ይሁን እንጂ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመሰረተ ድንጋይ ሲጣል፣ ለሀገራቸው በድጋሜ ታሪክ መስራት የሚችሉበት መልካም አጋጣሚ ተፈጠረ። “ቀኑ ደርሶ፤ ዓባይ ለእናት ሀገሩ ሊያድር የመሰረተ ድንጋዩ ሲቀመጥ፤ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የተሰማኝ ስሜት ላቅ ያለ ነበር፡፡ ይህን ግድብ ከእኛ ውጭ ማን ሊሰራው ይችላል ብዬ ቆርጬ ተነሳሁ። በመጀመሪያ ካለኝ 500 ብር ቦንድ በመግዛት ድጋፍ አደረኩ፡፡ ድጋፉን ስጀምር ሲኖረኝ ልደግፍ፤ ሳይኖረኝ ደግሞ ላቋርጥ በሚል አልጀመርኩትም፡፡ ተገድቦ እስከማየው ወይም እስከሚጠናቀቅ አቅሜ የፈቀደውን እደግፋለሁ በሚል ቃል በመግባት ነበር የተነሳሁት፡፡” ይላሉ አስር አለቃ ኃይለማርያም፡፡
በሚኖሩበት አካባቢ ባለው የወረዳ አስተዳደር እንደ ነዋሪ በተለያዩ ስራዎች ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉት ግለሰቡ፣ በተለይ የነዋሪዎች ፎረም ላይ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለትራንስፖርት ተብሎ የሚሰጣቸውን ገንዘብ ወደ ቤታቸው ይዘው ከመሄድ ይልቅ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ ነበር የሚያውሉት፡፡ ይህንን ሲያደርጉም ውስጣቸው ደስታ እንደሚሰማው ይገልፃሉ፡፡
የህዳሴው ግድብ ከተጀመረ አንስቶ ያለማቋረጥ በየዓመቱ ሲደግፉ መቆየታቸው የሚናገሩት አስር አለቃ ኃይለማርያም አራት ጊዜ ቦንድ ገዝተዋል፤ ቀሪውን ደግሞ በስጦታ መልክ ግንባታው እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፍ አድርገዋል፡፡
ሰዎች ደመወዝ ተቀብለው ለመሰረታዊ የቤት ወጪዎች ቢያውሉት አያስገርምም፤ የተለመደም ነው፡፡ አስር አለቃ ኃይለማርያም ግን ከጡረታቸው ላይ እየቀነሱ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይህንን ሲያደርጉ ሳይቸግራቸው ወይም ኑሮ አልጋ በአልጋ ሆኖላቸው ሳይሆን፤ “የእኔ ችግር ከሀገሬ አይበልጥም” በሚል ከሀገር ፍቅር ስሜት በመነጨ ነው፡፡
የ68 ዓመቱ ጎልማሳ የጡረታ ክፍያቸውን ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ሲያውሉ ባለቤታቸው በሚያገኙት ገቢ ነበር ኑሯቸውን የሚመሩት፡፡ “ባልና ሚስት ከአንድ ወንዝ…” እንዲሉ ባለቤታቸውም ዓባይ ተገድቦ የማየት ጉጉት ስለነበራቸው ከጎናቸው ሆነው ደግፈዋቸዋል፡፡
“ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቀው በሰንደቅ ዓላማዋ ነው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብንም ከሰንደቅ ዓላማዋ ለይቼ አላየውም። ኢትዮጵያን ከድህነት የሚያወጣ፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልክ እንደ ሰንደቅ ዓላማዋ እንድትታወቅ የሚያደርግ የኩራት ምልክት ነው፡፡ ይህ ስሜቴ ነው ያለኝን እንድደግፍ ያደረገኝ” ይላሉ፡፡ የእሳቸው ድጋፍ ብቻ በቂ ሆኖ ስላልታያቸውም የአካባቢው ነዋሪዎች ለግድቡ ግንባታ እጃቸውን እንዲዘረጉ በየቤቱ እየተንቀሳቀሱ ቅስቀሳና የማነሳሳት ስራ ሰርተዋል፡፡
በግድቡ ግንባታ ወቅት በተለይ የውሃ ሙሊቱ በሚከናወንበት ወቅት በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በኩል ሂደቱን ለማስተጓጎል የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች በኢትዮጵያ ላይ ተደርገዋል። ይህንን ጫና በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ ዲያስፖራ ኢትዮጵያውን በጋራ በመቆም ባደረጉት ትግል መመከትና በአሸናፊነት መወጣት ተችሏል፡፡ አስር አለቃ ኃይለማርያምም፤ “ኢትዮጵያ ግድቡን ከመገንባት ወደ ኋላ እንደማትል እምነቱም ነበረኝ፡፡ በኋላም የግድቡ ሙሌት እንደታሰበው በመከናወኑ ደስተኛ ሆኛለሁ፡፡” ይላሉ በወቅቱ የነበረው ወደኋላ መለስ ብለው በማስታወስ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከግንባታው ጀምሮ ያጋጥሙት የነበሩትን ውጣ ውረዶች አልፏል፡፡ ለበርካታ ዘመናት እንደማይቻል ተደርጎ ሲታሰብ የነበረው ሀገራዊ ህልም እውን በመሆኑም ኢትዮጵያውያንን አስደስቷል። አስር አለቃ ኃይለማርያምም፣ “ሳልሞት በህይወት ቆይቼ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቅቆ ለዚህ መብቃቱ በጣም ደስታ ነው የተሰማኝ፡፡ ለኢትዮጵያ ኩራትና አለኝታ ነው፡፡” ሲሉ ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
ለግድቡ ቦንድ የገዛ ከአምስት ዓመት በኋላ ገንዘቡን መውሰድ የሚቻል ቢሆንም ሻለቃ ኃይለማርያም ግን አሁንም እንደ የህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያን የሚያስጠራ ስራ ይሰራል የሚል ተስፋ ስላላቸው ብሩን የመውሰድ ሃሳብ እንደሌላቸው አጫውተውናል፡፡
በውስጥ አቅም፣ በብዙ ድካምና ጥረት እውን የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚያስተምረው ቁም ነገር ትልቅ መሆኑን አስር አለቃ ኃይለማርያም ይናገራሉ፡፡ “ኢትዮጵያውያን በራሳችን አቅም ዓባይ ላይ ግድብ መስራታችን ለአንድነታችን፣ ለህብረታችንና ለእድገታችን መሰረት ነው፡፡ ትልቁ ምኞቴ ኢትዮጵያ ከድህነት ወጥታ ካደጉ ሀገራት ተርታ ተሰልፋ ማየት ነው፡፡ ይህም ለእኔ ብቻ ሳይሆን መጪው ትውልድ በኩራት አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲሄድ የሚያደርግ ስራ ነው፡፡ ትውልዱ ከዚህ ትምህርት በመውሰድ ለሀገሩ ተግቶና ጠንክሮ መስራት ይኖርበታል፡፡” ሲሉም ይመክራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ሲባክን የነበረው ሃብት ለሀገሩ እንዲውል ወስኖ አንድነቱን ያሳየበት የህዳሴው ግድብ፤ “አይችሉም” ለሚሉ ሀገራት የብርቱነታችን ማሳያና ቀጣይ ለሚኖረውም ሌላ ትልቅ ስራ መነሻ እንደሚሆን አስር አለቃ ኃይለማርያም እምነታቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ጠንካራ ነው፡፡ ወደኋላ ከቀረንበት ወጥተን ፊት እየተጓዝን ነው፡፡ መጪው ትውልድም እንደ ሀገር የተያዘውን ትልም ተቀብሎ ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ወሬና ስንፍና ሀገርን አያሳድግም፤ ሀገርን የሚያሳድገው ስራ መስራት ነው ሲሉ ወጣቱ ሀገርን የመገንባት ኃላፊነቱን እንዲወጣ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
								 
															 
 
							 
							