የመዲናዋ የፕሮጀክት አፈፃፀም ምን ይመስላል?

You are currently viewing የመዲናዋ የፕሮጀክት አፈፃፀም ምን ይመስላል?

ዕለቱ ረቡዕ ነበር፡፡ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም፡፡ ጊዜው ለምሣ ሰዓት ተቃርቧል። መነሻቸውን አራት ኪሎ አድርገው ወደተለያዩ የአዲስ አበባ አቅጣጫዎች የሚጓዙ ታክሲዎች ፌርማታ ተገኝቻለሁ። የጉዞ አቅጣጫዬ ወደ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን ስለነበር፤ ከተደረደሩት ታክሲዎች መካከል ወደ ተረኛው ገባሁ፡፡ ታክሲው በመሙላት ላይ ነበር፡፡ ከኋላ ወንበር ጥግ ይዤ ተቀመጥኩ፡፡ እኔን ተከትለው ነጭ የሀበሻ ቀሚስ የለበሱ፣ ነጠላ የደረቡ እናት እና በእጇ የዕቃ መያዣ ዘንቢል ያንጠለጠለች ኮረዳ ወደ ታክሲው ገቡ። ከአጠገቤም ሠላም ብለውኝ ተቀመጡ። የእሳቸው ሠላምታ መስጠት፤ የእኔም አፀፋ መመለስ በአጭር ጉዞ ውስጥም ቢሆን በጥቂቱ ለማውራት በር ከፈተልን።

ተግባቢዋ እናት ድምፃቸውን ጎላ አድርገው ንግግራቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከእኔ ጋር ያውሩ እንጂ፤ ቀሪውን ሠው ጭኖ ወደ ፈረንሳይ ሌጋሲዮን በሚጓዘው ታክሲ ውስጥ ያሉ ተሳፋሪዎች ሁሉ ጆሯቸውን እንደሰጧቸው፤ ሌላ የጎንዮሽ ወሬ አለመኖሩ ምስክር ነው። እንዲህ አሉ፤ እጃቸውን አብራቸው ያለችው ኮረዳ ወደያዘችው ዘንቢል በማመላከት፤ “ኪዊንስ ለካ አራት ኪሎ መጥቷል? እኔ እኮ ዛሬ ነው ያየሁት። ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም መጥተን፤ ታክሲ ለመያዝ በእግር እየተጓዝን ነበር፡፡ የአራት ኪሎ በየዕለቱ መለወጥ አስደነቀኝ እና አጋጣሚውን በመጠቀም የእግር ጎዞዬን ወደ አደባባዩ ትንሽ አራዘምኩ።  እዛ ልንደርስ ስንል፤ አዲስ እና ግዙፍ የገበያ ማዕከል ተከፍቷል፡፡ ተያይዘን ወደ ውስጥ ገባን፡፡ በዚህ የገበያ ማዕከል ኪዊንስ ቅርንጫፍ ከፍቶ፣ ምርቶቹን ይዞ አገኘነው፡፡ ደስ አለኝ፡፡ ድንገት ብመጣም ባዶ እጄን አልመለስም ብዬ ይህንን ብርቱካን እና አቮካዶ ገዛሁ፡፡ ኪዊንስ አራት ኪሎ አለመኖሩ ይቆጨኝ ነበር። አሁን ከአራት ኪሎ እስከ ፈረንሳይ ላለነው ሠዎች ጥሩ ሆነልን” የሚለውን ሃሳብ በፍፁም ደስታ ገለፁ፡፡

እኝህ እናት ያለአንዳች ጎትጓች፣ ያለአንዳች ጥያቄ ይህንን የመሰለ ሃሳብ እንዲሰጡ ያደረጋቸው ምክንያት፤ በቅርቡ ለአገልግሎት የበቃው የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን፣ መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛ ፕሮጀክት ውስጥ በመገኘታቸው ነው፡፡ የአራት ኪሎ የገበያ ማዕከል የዚህ ፕሮጀክት አንድ አካል ሲሆን፤ በዚህ ውስጥ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ዕድሉን ካገኙ ተቋማት እና ድርጅቶች መካከል ሲናፍቁት የነበረውን ኪዊንስ ሱፐር ማርኬትን በማግኘታቸው ነው፡፡

በመሀል አራት ኪሎ፤ ከነባር ገፅታ ጋር ተወዳጅቶ፣ ዘመናዊነትን ከውበት ጋር አጣምሮ፣ ለዘርፈ ብዙ አገልግሎት ተሰናድቶ በቅርቡ በይፋ የተመረቀው የ4 ኪሎ የገበያ ማዕከልን፣ መኪና ማቆሚያን እና 4 ኪሎ ፕላዛ ፕሮጀክት፤ በ5 ሺህ 480 ካሬ ሜትር ላይ ማረፉን በመዲናዋ የሚከናወኑ ትላልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በኃላፊነት ሲመራ የቆየው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትላልቅ ፕሮጀክቶች ፅህፈት ቤት መረጃ ያመለክታል፡፡ (ፅህፈት ቤቱ አሁን ላይ ወደ አዲስ

አበባ ዲዛይንና ግንባታ ቢሮ መቀላቀሉን ልብ ይሏል፡፡)

የአራት ኪሎ ታክሲ ተርሚናልና ፕላዛ ፕሮጀክት በውስጡ በአንድ ጊዜ 8 ታክሲዎችን መጫንና ማውረድ፣ 126 ታክሲዎች ደግሞ እንዲቆሙ የሚያስችል የመኪና ማቆሚያ

(ፖርኪንግ) አለው። ሱፐር ማርኬቶች፣ ካፍቴሪያዎች፣ ኤቲ ኤም ማሽኖች፣ ጋዜጣ ማንበቢያና መሸጫ ሱቆች፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ሲስተም፣ ሦስት አሳንሰር፣ የደህንነት መቆጣጠሪያ ካሜራ፣ መዝናኛ ቦታዎችና የኢንተርኔት መጠቀሚያ ዋይ ፋይ የዚሁ ዘመናዊ ፕሮጀክት አካል ናቸው፡፡ ፕሮጀክቱ ለአገልግሎት ከበቃበት ዕለት አንስቶ ለነዋሪው በርካታ ጥቅሞችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የነዋሪውን ጥቅም ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን “ሠው ተኮር” የሚል መርህን በማንገብ እያከናወነ ይገኛል፡፡ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የልማት ሥራዎች ውጤታማነት አንደበት አውጥተው መናገር የሚችሉ ናቸው፡፡ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራው፤ መዲናዋ “ስምና ግብሯ ያልተወዳጀላት” በሚል ይሰነዘርባት የነበረውን ትችት በተጨባጭ ተግባሯ እንድትቀለብስ አግዟታል፡፡ ቀንና ሌሊት፣ ሳምንታትና ወራት እንዲሁም ዓመቱን ሙሉ ባልተቋረጠ መልኩ ለልማት ሥራ ላይ የማዋልን አዲስ ልምድ እየተገበረች ባለችው ከተማ፤ በየዕለቱ በሚባል ደረጃ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ይበቃሉ፤ አዳዲስ ግንባታዎች ይጀመራሉ፡፡ አሁን ይህ ሂደት ቀጥሏል፡፡

ሌላውን ትተን፤ በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁትን የመዲናዋ የልማት ፕሮጀክቶች ብንመለከት፤ በከተማዋ “ተዓምር”

የሚያስብል ተግባር እየተፈፀመ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ብቻ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ እናትዓለም መለሰ፤ ሰኔ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ተሰናድቶ በነበረ መድረክ ላይ ለጋዜጠኞች መግለፃቸው ይታወሳል፡፡

በመግለጫቸው እንዳብራሩት፤ ፕሮጀክቶቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ነው፡፡ ለግንባታቸውም ከ95 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 91 ቢሊዮን ብር  በመንግስት እና 4 ቢሊየን ብር  በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሸፈነ ነው፡፡ ይህ ውጤት የከተማ አስተዳደሩ በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ ከተያዘለት በጀት ውስጥ 71 በመቶ የሚሆነዉን ለካፒታል ፕሮጀክት ግንባታ እና ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራም እንዲውል በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን ማሳያ ነው።

በ2017 በጀት ዓመት ተጠናቅቀው ለአገልግሎት የበቁት ፕሮጀክቶች በቁጥር ብዛትም ሆነ በሚሰጡት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት በስኬታማነት የሚጠቀሱ ስለመሆናቸው በአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ብዙአየሁ ጉታ ይገልፃሉ፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በበጀት ዓመቱ ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች መካከል የመንገድ፣ የውሃ፣ የቤቶች ልማት፣ የመስሪያ ቦታዎች፣ የወጣቶች ስፖርት ማዘወተሪያ ሜዳዎች፣ የአረንጓዴ ልማት ሥፍራዎች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ከአጠቃላይ ለአገልግሎት ከበቁት ፕሮጀክቶች በቁጥር 16 የሚሆኑት ትላልቅ (ሜጋ) ኘሮጀክቶች ናቸው፡፡

16ቱን ትላልቅ ፕሮጀክቶች ብንመለከት ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ሀውልቶች፣ የአዲስ አበባን የቆየ የሥምና ግብር አለመገናኘት ችግር መፍቻ ቁልፎች፣

ሠው ተኮር የሚለውን መርህ አረጋጋጮች ናቸው፡፡ ለዚህ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከልን፣ የየካ ሁለት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ፓርኪንግን፣ የላፍቶ ቁጥር 2 የገበያ ማዕከልን፣ የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራን በማሳያነት መጥቀስ በቂ ነው። ፕሮጀክቶቹ እንኳን ለነዋሪው በሩቅ ላለውም እንደ ፀሐይ አብርተው የሚታዩ ናቸው፡፡

በ40 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈው የአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በቁርጠኛ የአመራር ብቃት ተጠናቅቆ በይፋ ለአገልግሎት የበቃው የካቲት 22 ቀን 2017 ዓ.ም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የተመረቀው ማዕከሉ፤ እስከ 1 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ አልጋዎችን የያዙ 2 ሆቴሎች፣ ከቤት ውጪ እስከ 50 ሺህ ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የኤግዚቢሽን ስፍራዎች ይዟል፡፡ በተጨማሪም፤ እያንዳንዳቸው ከ3 ሺህ እስከ 4 ሺህ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያላቸው 2 ትላልቅ አዳራሾች፣ በጠቅላላ እስከ 10 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግዱ 8 አነስተኛ እና መካከለኛ የመሰብሰቢያ አዳራሾች የማዕከሉ አካል ናቸው፡፡ ማዕከሉ ለመዲናዋ ብቻ ሳይሆን ለሀገር በርካታ ጥቅም እንደሚያስገኝ፣

ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የማስተናገድ አቅም እንደሚፈጥር፤ ለአገልግሎት ከበቃበት ማግስት ጀምሮ የአስተናገዳቸው ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ ሁነቶችን ማሳያ ናቸው፡፡

ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአገልግሎት የበቃው የየካ ሁለት የተሽከርካሪ ማቆሚያ፤ ለመዲናዋ እና ለነዋሪዋ በስጦታ ከተበረከቱ የ2017 በጀት ዓመት የልማት ውጤቶች መካከል ይጠቀሳል፡፡ የመኪና ማቆሚያው በመገናኛ እና በሾላ ገበያ መካከል የሚገኝ ሲሆን፤ ሁሉንም ማህበረሰብ ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ ታንጿል፡፡ ግንባታው በ5 ሺህ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን በአንድ ጊዜ ከ920 መኪናዎች በላይ የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ ሁለት ቤዝመንትና 5 ወለሎች ያሉት ይህ ፕሮጀክት፤ በእያንዳንዱ ወለሎች ላይ ያሉ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳይ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራና የእሳት አደጋ መከላከያ ያለው፣ የሰውና የተሽከርካሪ አሳንሰር የተገጠመለት፣ የአደጋ ጊዜ መውጫ በር ያለው፣ ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶችና አረንጓዴ ስፍራን ያካተተ ነው፡፡ በዚህም፤ እንደ ሀገር በዚህ ደረጃ ተገንብቶ ለአገልግሎት የበቃ የመጀመሪያው ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

ፕሮጀክቱን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፤ በዕለቱ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “የተሽከርካሪ ማቆሚያዎችን እና የትራንስፖርት ተርሚናሎችን ለማስፋፋት የምናደርገው ጥረት የህዝባችንን ኑሮ ለማሻሻል የምናደርገው ሥራ አካል ነው። የትራንስፖርት አገልግሎትን ማዘመንና ማሻሻል የብልጽግና ጉዟችን መሰረት ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩ ዘርፉን ለማሻሻል ትኩረት አድርጎ እየሠራ ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የከተማዋ ነዋሪዎች የኑሮ ውድነት ጫና ጉዳት እንዳያደርስባቸው ለማድረግ በከተማ አስተዳደሩ ከተሠሩና እየተሠሩ ካሉ በርካታ ሥራዎች መካከል፤ የአምራች እና ሸማች ቀጥተኛ ግንኙነት እንዲፈጠር የሚያግዙ ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት የበቁበት ተግባር በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል። በሁሉም የአዲስ አበባ መግቢያ በሮች እያገለገሉ ያሉት የገበያ ማዕከላቱ፤ እንደ ሀገር በ2010 ዓ.ም. ከመጣው ለውጥ በኋላ የተገነቡ ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ደግሞ፤ እንደ ከተማ 5ተኛ የሆነው  የላፍቶ ቁጥር 2 የገበያ ማዕከል ለአገልግሎት በቅቷል፡፡ ይህ ግዙፍ እና ዘመናዊ የገበያ ማዕከል 8 ነጥብ 8 ሄክታር ላይ የተገነባ ሲሆን፤ በውስጡ 159 ሰፋፊና ምቹ ሱቆች፣ 9 የጅምላ ማከፋፈያዎች እና 2 ሞሎችን ይዟል፡፡

በተጠናቀቀው የ2017 በጀት ዓመት ሠፊ የሆነ የኮሪደር ልማት ተከናውኗል፤ ሂደቱም ያለማቋረጥ ቀጥሏል፡፡ በበጀት ዓመቱ ለአገልግሎት ከበቃው ግዙፍ የኮሪደር ልማት ሥራ የተገኘውን ውጤት ለመመልከት ዓይንን በጥቂቱ ከፍቶ ማስተዋል ይበቃል፡፡ ካስተዋልን እልፍ ውጤቶችን እንመለከታለን፡፡ ከእልፍ ውጤት መካከል አንድ ምሳሌ ይጠቀስ ከተባለ ደግሞ፤ የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ሥራን ማንሳት ይቻላል። ይህ የካዛንቺስ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራ፤ የ1000 ሄክታር መሬት ሽፋንን ይዟል፡፡  በውስጡም 40 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ ዝርጋታ፣ 81 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገድ ግንባታ፣ 20 ነጥብ 7 ኪሎ ሜትር የሳይክል መንገድ፣ 15 የህጻናት መጫወቻ ቦታዎች፣ 8 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ 16 የህዝብ መዝናኛ ፕላዛዎች እና አረንጓዴ ፓርኮች፣ 19 የመጸዳጃ ቤቶች፣ 105 የንግድ ሱቆች፣ 40 የመኪና ማቆሚያዎች እና ተርሚናሎችን በማካተት ለአገልግሎት በቅቷል፡፡

የካዛንቺስ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራ፤ በኮሪደር ልማት ምክንያት የሚነሱ የከተማዋን ነዋሪዎች ለጉዳት የማይዳርግ፤ ይልቁንም የበለጠ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመሆኑ ሁነኛ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ ይህንን ለመረዳት ፕሮጀክቱ በይፋ ለአገልግሎት በበቃበት ወቅት የአዲስ አበባ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ያስተላለፉትን መልዕክት ማስታወስ ይገባል፡፡ እሳቸው በመልዕክታቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል፤ “ከአካባቢው በልማት ለተነሱ ነዋሪዎች ምቹ የመኖሪያ ቤት ተገንብቶ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም፤ 105 ሱቆችን በመገንባት ከዚህ ቀደም በአካባቢው በልማት ለተነሱ ነጋዴዎች እንዲሁም ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለተመረቁ ሴቶች አስተላልፈናል” የሚለው ይገኝበታል፡፡

የካዛንቺስ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ሥራ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ከሚችሉ ግዙፍ እና ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች አንዱ ስለመሆኑ፤ ፕሮጀክቶቹ ለአገልግሎት በበቁበት ወቅት በቦታው የተገኙትን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ምን መልዕክት አስተላለፉ የሚለውን ማስታወስ ጠቃሚ ነው፡፡ እሳቸው በመልዕክታቸው፤ “ከተሞቻችንን የማዘመን ሰፊ ጥረት አይነተኛ ማሳያ የሆነውን በካዛንቺስ ያለውን የኮሪደር ልማት በይፋ መርቀናል። የተጎሳቆሉ እና በእጅጉ የተጎዱ ቤቶች እና ከባቢ መገኛ የነበረው ካዛንቺስ ዛሬ የጋራ ጥረት እና ለውጥ ሽልማታችን ሆኖ ተገኝቷል። ከዚሁ አካባቢ ተነስተው ለማኅበረሰባችን የከበረ የኑሮ ሁኔታን ለመፍጠር ያለንን ፅኑ እምነት እና ተግባር በሚያሳይ አኳኋን ለኑሮ ወደ ተሻለ ከባቢ የተዛወሩትን ነዋሪዎች ከጥቂት ቀናት በፊት ጎብኝተን ነበር። የተዛወሩበት ከባቢ እጅግ ምቹ መሆኑን አይተናል። ዛሬ ደግሞ የተነሱበትን ሰፈር ድንቅ የኮሪደር ልማት ሥራ መርቀናል” ነበር ያሉት፡፡

አያይዘውም፤ ትላንትን ከዛሬ፣ ዛሬን ከነገ ያስተሳሰረ ሃሳብ ከካዛንቺስ የኮሪደር ልማትና መልሶ ማልማት ሥራ ጋር በማስተሳሰር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስተላለፉትን መልዕክት በመጥቀስ ጽሑፋችንን እንቋጭ፤ “በአስደናቂ አጭር ጊዜ የተጠናቀቀው የካዛንቺስ ለውጥ ለዘመነ ከተማ ልማት ሥራችን ለአረንጓዴ፣ ንፁህ እና ዘመናዊ የከተማ ማዕከላት ያለንን ርዕይ ግዘፍ ነስቶ በማሳየት መሠረት የሚጥል ነው። በዚህ ግዝፈት የሚከወኑ ሥራዎች ሰፋ ያለ ጥረት ይሻሉ። ጊዜያዊ ምቾት ፈተናዎችንም ሊያስከትሉ ይችላሉ። ነገር ግን ለታላቁ የሀገር ጥቅም የሚከፈሉ አስፈላጊ መስዋዕትነቶች ናቸው። ይህ የእድገት መንገድ መቀጠል ያለበት ነው። የታደሰ ተስፋ ይሰጣልና። በተለይ ለልጆቻችን ነገ።

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review