ያለነው በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘመን ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ በዓለም ላይ የዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪነት እያየለ በመምጣቱ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለሀገራት የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂን መጠቀም የውዴታ ግዴታ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ስለዚህ ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአሠራር እና ዘመኑ በሚጠይቀው ሁሉ ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ዘርፉን ለመጠቀም እንቅስቃሴ ከጀመረች ሰነባብታለች፡፡ በሂደትም፤ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ውጤቶችን እና አሠራሮችን ከመጠቀም አልፋ በራስ አቅም ቴክኖሎጂዎችን አልምታ እስከመጠቀም የደረሰችባቸው መስኮች እንዳሉ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህን ከዚህም በላይ ለማጎልበትም የተለያዩ ስራዎች መስራቱን ቀጥላበታለች፡፡ የኮደርስ ስልጠና ደግሞ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡
በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስታት ትብብር እየተተገበረ ባለው የ5 ሚሊዮን ኮደርስ ንቅናቄ በርካቶች ተጠቃሚ ሆነዋል፤ በመጠቀም ላይ የሚገኙም አሉ። ስልጠናው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑ ሙያተኞችን በብዛት ለማፍራት ከማገዝ በተጨማሪ፤ የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ትልቅ አቅም እንደሚሆን ንቅናቄው ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ ጉዳዩን አስመልክቶ በሚተላለፉ መልዕክቶች በተደጋጋሚ ሲነገሩ ይደመጣል፡፡ ይህንን መልካም ዕድል ቀድመው በአግባቡ የተጠቀሙ ሥልጠናዎቹን መውሰድ የቻሉት አንድና ከዚያ በላይ ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት (ሰርተፊኬት) መያዝ ችለዋል፡፡ በዚህ ፅሑፍም ዕድሉን ከተጠቀሙ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች መካከል የተወሰኑትን በ2018 ዓ.ም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ስለፈጠረላቸው መነቃቃትና አቅም ሀሳባቸውን ለዝግጅት ክፍላችን አጋርተዋል፡፡
ወጣት ዮናታን ሃይሉ ይባላል፡፡ በድህረ ገፅ ዲዛይነር እና ኮምፒዩተር ማኔጅመንት ሲስተም ዲፕሎማውን ከጀነራል ዊንጌት ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ አግኝቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአንድ የግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የኮደርስ ስልጠና እድል መመቻቸቱን እንደሰማ ወዲያው ነበር ስልጠናውን መውሰድ የጀመረው። በተለይም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) እና የድረ ገፅ (የዌብ ፕሮግራሚንግ) ስልጠና ወስዷል። ሁለቱንም ስልጠናዎች ለማጠናቀቅ 5 ሳምንታትን ብቻ እንደወሰደበትም ተናግሯል፡፡
“መንግስት ይህንን ዕድል ማመቻቸቱ ሊያስመሰግነው ይገባል፡፡ ለሁሉም እኩል ዕድልን የሰጠ፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚጨምር፣ የአጭር ጊዜ ስልጠናን በነጻ ማመቻቸት መቻሉ ለእኛ ወጣቶች ከአዳዲስ እውቀትና ክህሎት ጋር እንድንላመድ ያስችለናል። እንደነዚህ ያሉ ስልጠናዎችን በራሳችን እንሰልጥን ብንል ወጪው ቀላል የሚባል አይደለም” የሚለው ወጣት ዮናታን፤ ከዚህ ቀደም በኦንላይን ስልጠናዎችን ለመከታተል እንደሞከረ እና ከፍፃሜ ለማድረስ እንዳልቻለ አውስቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ስልጠናውን ለመውሰድ የሚጠየቀው ገንዘብ ከአቅሙ በላይ እንደሆነበት አልሸሸገም፡፡
“አዲስ አበባ የስማርት ሲቲን ፅንሰ ሃሳብ ተግባራዊ በማድረግ ላይ የምትገኝ ከተማ ነች” የሚለው ወጣት ዮናታን፣ የከተማዋን ዕቅድና ዓላማ ለማሳካት ከሚያስችሉ አቅሞች መካከል በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ብቁ የሆነ የሠው ሃይል ቁጥርን ማበራከት አንዱ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የ5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና እገዛ ያደርጋል። ምክንያቱም በቴክኖሎጂ ራሱን ብቁ ያደረገ ዜጋ አገልግሎት አሰጣጦችን በሙሉ በቴክኖሎጂ በመደገፍ ቀልጣፋ የአሠራር ስርዓት መከተል ስለሚያስችል ሲል አብራርቷል፡፡
“ስልጠናው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መሆኑ እኛንም ብቁ ተወዳዳሪ እንድንሆን ያግዘናል፡፡ በያዝነው 2018 ዓ.ም. በሥራው ውጤታማ በመሆን ዓለም ተመራጭ እና ተፈላጊነትን ለማትረፍ ራሴን በአዳዲስ ዕውቀቶችና ክህሎቶች የማዳበር ተግባር ላይ ትኩረት ለማድረግ አቅጃለሁ፡፡ በ5 ሚሊዮን ኮደርስ ከተዘጋጁት የሥልጠና መርሃ ግብሮች መካከል የተቀሩትን ኮርሶች የመጨረስ ውጥንም አለኝ፡፡ አዳዲስ ልምምዶችን ወደ ህይወታችን ባስገባን ቁጥር የበለጠ ሌሎች ነገሮችንም ለማወቅ እንድንበረታታ ያግዘናል”ም ብሏል፡፡
“በማህበራዊ ሚድያዎች ላይ የምናጠፋውን ጊዜ ቆጠብ በማድረግ የተለያዩ ራስን የማብቂያ ስልጠናዎችን በመሰልጠን አንድ እርምጃ የተሻልን ሰዎች መሆን ይጠበቅብናል” የምትለው ደግሞ ወጣት የምስራች አሰፋ ናት። ወጣቷ በእሳትና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፤ በኤክስኪዩቲቭ ፀሐፊነት ሙያ እያገለገለች ሲሆን፤ የ5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዕድልን መጠቀም ችላለች፡፡ የኮደርስ ስልጠናን ለመውሰድ የፈለገችበትን ምክንያት ስታስረዳም፤ “የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ተማሪ መሆኔ፣ በኮደርስ የተዘጋጁትን ስልጠናዎች መውሰድ ባለኝ ዕውቀትና ክህሎት ላይ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥርልኝ በማመኔ ነው” ብላለች።
“የማባክነው አልያም እንደዋዛ የማሳልፈው ጊዜ ስለሌለ፤ አራቱንም የስልጠና ፓኬጆች (መሰረታዊ ኘሮግራሚንግ፣ ዳታ ሳይንስ፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት እንዲሁም አንድሮይድ ኘሮግራሚንግ) ስልጠናን በ20 ቀናት ውስጥ በመውሰድ ማጠናቀቅ ችያለሁ” የምትለው ወጣት የምስራች፤ ላጠናቀቀቻቸው አራቱም የስልጠና ዓይነቶች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) ወስዳለች፡፡ እንደ ወጣቷ ገለጻ፣ እነዚህን አዳዲስ ስልጠናዎች መውሰዷ በሥራ አካባቢዋ ተወዳዳሪና ብቁ ሆና ለመቅረብ አስችሏታል፡፡
በአዲሱ ዓመት ስለያዘችው ዕቅድ አስመልክቶ ወጣት የምስራች፤ “በ2018 ዓ.ም. በስራዬ ውጤታማ ከመሆን ባሻገር ያገኘሁትን እውቀት ለሌሎች ማጋራት እንዲሁም የኮደርስ ስልጠና ለመውሰድ የሚፈልጉትን በሀሳብ የማገዝ ፍላጎት አለኝ፡፡ በተለይ ሴቶች እራሳቸውን ለማብቃት አዳዲስ እውቀት እና ክህሎት የሚያስጨብጡ፣ ተወዳዳሪነትን የሚጨምሩ ስልጠናዎች ላይ መሳተፍና ራሳቸውን ማብቃት አለባቸው፡፡ የሴቶች ብቁ ሆኖ መገኘት፤ ከራሳቸው አልፎ ለቤተሰብ፣ ለማህበረሰብ እና ለሀገር ትልቅ ጥቅም ያስገኛል፡፡ ስለዚህ እንደሴትነቴ ራሴን የበለጠ ብቁ ለማድረግ፣ ሥራዬን በውጤታማነት ለማከናወን እና ሌሎችን ለማበረታታት አዲሱን ዓመት በመልካም ሁኔታ ለመጠቀም አቅጃለሁ፡፡” ብላለች፡፡
በስልጠናው ተጠቃሚ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት ኤደን ቦጋለ ሌላኛዋ ነች፡፡ ይህች ወጣት በቢዝነስና ማኔጅመንት ትምህርት ዘርፍ ዲግሪዋን ከሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ አግኝታለች፡፡ በገንዘብ ቢተመን ቀላል የማይባል ወጪ ይጠይቅ የነበረውን የኮደርስ ስልጠና በመውሰድም ራሷን ለስራ ዝግጁ እያደረገች ትገኛለች፡፡ ትምህርቱ በነፃ ቢሆንም መንግስት ትልቅ ተግባቦትን በመፍጠር ለዜጎች ያመቻቸው እድል ሆኖ እንዳገኘችው ተናግራለች። መሰረታዊ የኮምፒዩተር እውቀት እንዲሁም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ያላቸው ሰዎች በቀላሉ መማር የሚችሉት ስልጠና መሆኑንም ከልምዷ በመነሳት አስረድታለች፡፡
ወጣት ኤደን አክላ እንደተናገረችው፤ በነፃ ነገር ግን ዋጋው ቢተመን እጅግ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ስልጠና በቀላሉ ማግኘት መቻል ትልቅ ፋይዳ አለው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራት ከተቀረው ዓለም ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ወሳኝ ነው፡፡ በርካታ የዓለም ሀገራት እንደ ኮደርስ አይነት ስልጠናዎች በቂ ግንዛቤ አላቸው፡፡ ሀገራችንም የዚህ እድል ተቋዳሽ መሆን መቻሏ ከተቀረው የዓለም ህዝብ ጋር እኩል ለመራመድ ያስችላታል፡፡
ከዚህ በፊት በግሏ የተለያዩ ስልጠናዎችን በድህረ ገፅ ለመማር ብትፈልግም ሂደቱ አዳጋች ሆኖ በማግኘቷ እንዳልተማረች ያስታወሰችው ወጣት ኤደን፤ በ2018 በጀት ዓመት የተቀሩትን ሁለት ስልጠናዎች በመውሰድ አሁን ካለችበት የእውቀት ደረጃ ከፍ በማለት ተወዳዳሪነቷን ለማሳደግ እንደምትሠራ አብራርታለች፡፡ በቀጣይ ሌሎች የስልጠና ፓኬጆች ተዘጋጅተው ዜጎች የእውቀት ባለቤት እንዲሆኑ እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን እንዲያተርፉ ቢደረግ መልካም ነው ስትልም ሃሳቧን ሰጥታለች፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አዋሌ መሐመድ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሀገራችን በቴክኖሎጂው ዘርፍ የተሠሩ ሥራዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ መንግስት ዜጎችን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማስቻል 5 ሚሊዮን ኢትዮ ኮደርስ የተሰኘውን ስልጠና በማመቻቸት በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል፡፡
“የ5 ሚሊዮን የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ዜጎች በዲጅታል ኢኮኖሚ ውስጥ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ የስማርት ሲቲ ርዕይ እንዲሳካ፣ አዳዲስ የሥራ እድሎች እንዲፈጠሩ፣ ከተማችንን ብሎም ሀገራችንን በኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ ውጤታማ ለማድረግ እንዲሁም ለፈጠራ ምቹ ሁኔታን ለማመቻቸት ትልቅ ዕድልን ፈጥሯል” የሚሉት ቢሮ ኃላፊው፤ የኮደርስ ስልጠናው ከስድስት እስከ ስምንት ሳምንት የሚወሰድ መሆኑን በመጠቆም፤ ወጣቶች ያላቸውን ጊዜ አልባሌ ቦታ ከማሳለፍ በመቆጠብ፣ ሠራተኞችም የእረፍት ጊዜያቸውን በመጠቀም ክህሎታቸውን የሚያዳብሩበት የስልጠና መርኃ ግብር በመሆኑ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሐምሌ 2016 ዓ.ም. በይፋ ያስጀመሩት የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና መርኃ ግብር፤ በሦስት ዓመታት ውስጥ አምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ የዲጂታል ክህሎት ማስጨበጥን ያለመ ነው። የስልጠና መርኃ ግብሩ በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለፃ፤ የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ስልጠናውን መውሰድ መቻላቸው ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ ነው፡፡ መርኃ ግብሩ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን ባሉት ጊዜያት (ይህ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ) በከተማዋ ሁለት መቶ ሺህ ሰልጣኞች ስልጠናውን ወስደው አጠናቅቀዋል። በተለይ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎች ስልጠናውን በፍቃደኝነት መውሰድ መቻላቸው መሰረት የጣለ የአሠራር ስርዓት ለመከተል ያስችላል። ሰራተኞችም ቢሆኑ የኮደርስ ስልጠና መውሰዳቸው ውጤታማ ስራዎችን ለማከናወን በእጅጉ ያግዛል፡፡
በሄለን ጥላሁን