አዲስ ዓመት ሲመጣ ምን ተመኝታችሁ ምን አሳክታችሁ ታወቃላችሁ ? በዘንድሮው አዲስ ዓመትስ ምን አቀዳችሁ ፡-
አዲስ ዓመት አዲስ ነገርን ከማየት እና ከመመኘት እንዲሁም ከመጠበቅ ጋር ልዩ ቁጥርኝት አለው ፡፡
አዲስ የሚለው ነገር ከስነ-ልቦና ዕይታ አንፃር ከዚህ በፊት ያልነበረ ያልተደረገ ወይንም ያላየነውን ለማየት ያልሰማነውን ለመስማት እና ወደፊት ለማድረግ እና ሆኖ ለማየት እንችላለን ብለን እንድናስብ የሚያደርግ ትርጉም እንደሚሰጥ የስነ ልቦና ባለሞያው አቶ ጌታቸው ሙላት ከኤ ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ነግረውናል ፡፡
ከዚህ በመነሳት አይምሯችን ስላማያውቀው ነገር ነገን ጥሩ አድርገን እንድንስል በተስፋ በምኞት እንድንጠብቅ እንድናስብ ዕድል ይሰጠናል ነው ያሉት ባለሞያው ፡፡
አዲስ እና አሮጌ የአዕምሮ የሃሳብ ልዩነት ናቸው ያሉት አቶ ጌታቸው ፡፡ በአሮጌው ዓመት ያልተጠቀምነውን ወይንም ያላሳካነውን መለስ ብለን እንድናይ በቀጣይ የምናቅደውን ደግሞ በተስፋ በምኞት ለመተግበር እንድነዘጋጅ አዲሱ ዓመት ዕድል እንደሚሰጥ ነግረውናል ፡፡
በዚህ መክኒያት ሁሌም አዲስ ዓመት ከዕቅድ ጋር ይያያዛል ፡፡ በአዲስ ዓመት ከሚበላ ከሚጠጣ እና ከሚለበሰው የዘለለ መሆን አለበት ያሉት አቶ ጌታቸው የሰው ልጅም ከሌሎች ፍጥረት የሚለየው ነገሮችን ለመከወን ምክኒያት የሚፈልግ በመሆኑ አዲስ ዓመትም አንዱ ክስተት ስለሆነ ዘመኑን ስንቀበል አዲስ ዕቅድ በማውጣት እና በማዘጋጀት ነውይህም ባህል እየሆነ መጥቷል ሲሉ ነው የተናገሩት ፡፡
ዓዲስ ዓመትን ጠብቆ ዕቅድማዘጋጀት ባህል ይሁን እንጂ የተዘጋጀውን ዕቅድ በቀናት እና በሳምንታት ውስጥ የመተው እና የመርሳት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል ሰለሆነም እንደ ግለሰብ የምናቅደው ዕቅድ የሚተገበር የሚጨበጥ እና ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሸጋግረን ሊሆን እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተው ነው ባለሞያው የገለፁት ፡፡
ዕቅድ በተለያየ ወቅት ሊታቀድ ይችላል ነገር ግን ሌሎቹ ቀናት እና በዓላት የዘመን መስፈሪያ አይደሉም ያሉት የስነ-ልቦና ባለሞያው አዲስ ዓመት ላይ ግን ሽግግር አለ ሲሉ ነው የገለፁት ፡፡
ወደ አዲስ ምዕራፍ ስንሸጋገር አዲስ ተስፋ አዲስ የመለወጥ ፍላጎት አብሮ ይመጣል ያድጋል ይህንን ተጨባፅ ለማድረግ ደግሞ በዕቅድ ሊደገፍ ይገባል ስለሆነም የማወጣው ዕቅድ የጊዜ ገደብ የተቀመጠለት እና የመፈፀም ዓቅማችን እና የስነ-ልቦና ዝግጅታችንን ማዕከል ያደረገ ሊሆን እንደሚገባው ነው ባለሞያው የገለፁት ፡፡
በሰው ልጅ ህይወት የማያቋርጠው ነገር ለውጥ ነውያሉት ባለሞያው ብናቅድም ባናቅድም በአዎንታም በአሉታም በህይወታችን ለውጥ መከሰቱ አይቀርም ነገር ግን በታቀደ ዕቅድ የሚመጣ ለውጥ ጠንካራ ስነ-ልቦና እንዲኖረን እና የተግባር ሰው እንድንሆን ያግዛል ያሉት የስነ-ልቦና ባለሞያው አቶ ጌታቸው ሙላት የተቀበልነውን አዲስ ዓመት ከራስ ጋር በመነጋገር በደስታ በተስፋ የሚጨበጥ እና የሚተገበር ዕቅድ በማዘጋጀት እና በመተግበር ልንጀምረው ይገባናል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡
በያለው ጌታነህ