AMN – መስከረም 2/2018
የዓለም ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ረዳት ዋና ጸሀፊ ቶማስ አሳሬ እንደገለፁት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የአየር ንብረት ፋይናንስ በማመንጨት እና ጎረቤት ሀገራት በታዳሽ ኃይል በማስተሳሰር የጎላ አበርክቶ አለው፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጀመረቻቸውን ኢንሼቲቮች በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር እንደሚገባም የተቋማቱ መሪዎች ገለፀዋል፡፡ የአፍሪካ የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ከአራት በመቶ ባይበልጥም በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ከፍተኛ ተጎጂ መሆኗ አልቀረም፡፡
በተለይም አፍሪካን ጨምሮ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ የሚደርስባቸውን ችግር የህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ሆኗል፡፡ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የጎላ በካይ ጋዝ ከሚለቁ ሀገራት ከመጠበቅ የራሷን መፍትሔ መፈለግ አለባት የሚለው የብዙ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምክረ ሀሳብ ነው፡፡

የዓለም የእርሻና ምግብ ድርጅት ረዳት ዳይሬክተር ጀነራል እና የአፍሪካ ተጠሪ አበበ ኃይለገብርኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስን ከፍተኛ በካይ ጋዝ የሚለቁት ያደጉ ሀገራት እንዲሸፍኑ የወጡ የፓሪስ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በአግባቡ ገቢራዊ አልተደረጉም ብለዋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት በደቡብ ደቡብ ትብብር ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡ አፍሪካ የታዳሽ ሀይል፣ እምቅ የማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ጸጋዎች ያሏት አህጉር መሆኗን በመጥቀስ፤ በደቡብ ደቡብ ትብብር ጸጋዋን የምትጠቀምበት ቴክኖሎጂ ማላመድ አለባት ብለዋል፡

የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የደቡብ ደቡብ ትብብርን በማጠናከር የቴክኖሎጂ አቅማቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በቢሊዬን የሚጠቀሱ ችግኞችን በመትከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ እየገነባች መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአመራር ቁርጠኝነት እና የኢትዮጵያ ህዝብ ተሳትፎ የላቀ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡