AMN- መስከረም 02/2017 ዓ.ም
የነፃነት ምድር፤ የአይበገሬነትም ምሳሌ ናት። ኢትዮጵያ። ፈተናዎች በታሪክ ተለይተዋት አያውቁም። ችግር በእጦትና በረሀብ ወገቧን አጉብጦም ያውቃል።
ጠላትም ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅሞ አንድነቷን እና ሉዓላዊነትን ደጋግሞ ፈትኗል። መልክ እየቀያየሬ ያዳከማት ችግር ሁሉ ተደምሮ ሊያጠፋትም ሊያፈርሳትም አልቻለም። ይልቁን በችግር ውስጥ ተቋቁሞ ማለፍ የቻለ ሀገር እና አንድነቱን የጠበቀ የጠንካራ ህዝብ ተምሳሌት ሆነች እንጂ።
ኅብራዊነትን በአድዋ ያፀኑ ጀግኖች ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ ዛሬም በዓባይ ወንዝ ላይ ዳግም የአንድነት አሻራ የሆነውን እና ግዙፉን ግድብ በመገንባት ታሪክ ሰሪነቷን ቀጥላለች። በዚህም የተፈጥሮ ሀብትን በአግባቡ አልምታ ከድህነት መውጫዋን ያበጀች ሀገር ለመሆን ችላለች ።
ይህ ብርቅዬ ማዕድናትን ጨምሮ የተፈጥሮ ፀጋዎችን የታደሉ ነገር ግን ከድህነት ማምለጫ በሩ ለጠፋቸው ደሀ ሀገራት ዓርዓያ የሚያደርጋትም ነው።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ምንም እንኳ ከጅምሩ ሀሳቡ ያልተዋጠላቸው ሀገራት እና ኃይሎች ቢኖሩም በየወቅቱ ፈተናን ከመደቀን ውጭ ውጥኗን ከግ ከማድረስ እንዳላገዷት ዛሬ ላይ ያለን ኢትዮጵያዊያን ህያው ምስክሮች ነን።
ግዙፉን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር ኢ/ር) ግድቡ የተገዳደሩ ሁለት መልክ ያላቸውን ተፅኖዎች ያነሳሉ።
አንደኛው ተፅዕኖ የሚነሳው የቅኝ ዘመን ስምምነቶች ጥሩ ናቸው ብለው ከሚምኑ እና ሀሳቡን ከሚያቀነቅኑ ኃይሎች ነው።
ሁለተኛው ከታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የሚነሳ ተገቢ ያልሆነ የጥቅመኝነት አባዜ እንደሆነ ይገልፃሉ ። ታዲያ ኢትዮጵያ ለትብብር እና ለድርድር በሯን ክፍት በማድረግ ኋላ ቀሩን እሳቤ ድል ማድረጓን ይናገራሉ።
አካሄዱ ተገቢ ያለው የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በሉዓላዊ ሀገር ላይ ለመጫን የሚደረግ ጥረት እና ሀብታችንን ለመቀማት የተደረገ ነውም ብለዋል አምባሳደሩ።

ስለ ግድቡ እውነታን ማስረዳት፣ ፋይዳው ሀብት መፍጠሪያ፣ ከድህነት መውጫ እና የህዝብ ተጠቃሚነትን ማሳደጊያ መሆኑን ማስገንዘብ ኢትዮጵያ የተከተለችው አካሄድ መሆኑንም ተናግረዋል ።
የህዳሴ ግድብ የጸጥታው ምክር ቤት የደረሰ ጉዳይ እንደነበር አስታውሰው በመሆኑም ከሀገር ውስጥ ጀምሮ እስከ አፍሪካ ህብረት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እውነቱን በትክክል እንዲገነዘብ ማስቻል ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ብስለትን ያሳየ ነው ብለዋል ።
በተለይም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተመራውን ብቃት ያለው ዲፕሎማሲን በአብነት ጠቅሰዋል። አሁን የተሽሞነሞነው የህዳሴ ግድብ የዚሁ ስክነት እና ብስለት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ስኬታችን ማረጋገጫ ነው ብለዋል አምባሳደሩ።
በሀገር ውስጥ እና በውጭ የሚኖሩ ከህፃን እስከ አዋቂ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አምባሳደር ሆነው በሀገር ጉዳይ በግንባር ቀደምትነት መሰለፋቸውም ትልቅ ሚና እንደነበረው አስታውሰዋል።
እንደ ሀገር ወደፊትም ብዙ የዲፕሎማሲ ሥራዎች እንደሚኖሩ ያነሱት አምባሳደር ስለሺ በአሁኑ ወቅት በአፍሪካ ትልቁን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ገንብተናል ሲሉ ተናግረዋል።
ግድቡ በየዓመቱ በጎርፍ ጉዳት የሚደርስባትን ሱዳንን ከተመሳሳይ ችግር ይታደጋል ያሉት አምባሳደር ስለሺ ከእንግዲህ መተባበር ለሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት አስፈላጊ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ለግድባችን ስኬት የገንዘብ፣ የዲፕሎማሲ፣ ድምፅ የማሰባሰብ እና ሳይንሳዊ ጽሑፎችን በማዘጋጀት ታሪካዊ ሃላፊነት የተወጣችሁ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ እንኳ ደስ አለን ብለዋል አምባሳደር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ።
በማሬ ቃጦ