AMN – መስከረም 2/2018 ዓ/ም
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለምረቃ መብቃቱን አስመልክቶ ‘’በህብረት ቆመናል በህብረት ችለናል‘’ በሚል መርህ የብዙሀን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስተባባሪነት ተካሄዷል፡፡
ነዋሪዎች፤ የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በትጋት እንደሠሩት ሁሉ የምርቃት ቀኑን በጉጉት ሲጠባበቁ እንደነበር አውስተው፤ የግድቡ መጠናቀቅ የፈጠረባቸውን ደስታ ለመግለጽ በመስቀል አደባባይ የአካል ብቃት እንቅስታሴ አካሄደዋል፡፡
እኛ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ህዳሴ ግድብን እውን ማድረግ መቻላችን፤ ለአለም ትልቅ ትምህርት ያስተላለፈ እና ለታሪክ ተሰንዶ የሚቀመጥ የዘመናችን ዳግማዊ አድዋ ነው ሲሉም ገልፀዋል፡፡
ግድቡ ለቀጣዩ ትውልድ ትልቅ ተስፋ ነው ያሉት ነዋሪዎቸ፤ ሰንደቅ አላማችንን ከፍ የሚያደርግ እና እንደ ሀገር በዘመናችን ትልቅ ሥራ ሰራን ብለን የምናወራው የጋራ ታሪካችንም ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ብቻ አይደለም ያሉት ነዋሪዎቹ፤ የላብና የደም አሻራ ያረፈበት የድል አድራጊነትና የአሻናፊነት ምስክር ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
እስከዛሬ በአያቶቻችን ታሪክ ነበር የምንኮራው ያሉት ነዋሪዎቹ፤ ዛሬ ላይ አያቶቻችን በአድዋ የተጐናፀፉትን ድል፤ እኛም ደግመን የይቻላል መንፈሰ ማሣያ የሆነውን የታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባታችን ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው ብለዋል፡፡
በህዳሴ ግድብ የታየው የመልማት ቁጭት፣ አንድነትና መነሳሳት በሌሎችም የልማት መስኮች በተባበረ ክንድ ልንደግማቸው ይገባልም ሲሉ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በ በረከት ጌታቸው